ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ለማድረግ እየሰራች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ለማድረግ እየሰራች ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ለማድረግ እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ የአውሮፓ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ዩኖ ኦማርጄን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) የአውሮፓ ፓርላማ ምክትል ፕሬዝዳንት ጉብኝት የኢትዮጵያና የአውሮፓ ሕብረት ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚረዳ በመግለጽ ሕብረቱ የረጅም ጊዜ የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኑን ተናግረዋል።
ሁለቱ ወገኖች በብዙ መስኮች የጋራ ጉዳዮች አሏቸው ያሉት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ለማድረግ እየሰራች መሆኑንና የፖሊሲ አቅጣጫዋም ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር መሆኑን አስረድተዋል።
ከሚኒስቴሩ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዩኖ ኦማርጄ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት የረጅም ጊዜ መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያም የሕብረቱ ቁልፍ አጋር መሆኗን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና ደኀንነት መጠበቅ ከፍተኛ ሚና አላት ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሕብረቱ ግንኙነቱ ን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) በቀጣናዊ እና አካባቢያዊ ወቅታዊ የሰላም እና ደኀንነት ሁኔታዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገውላቸዋል።