ቀጥታ፡

በክልሉ በሽታዎችን ቀድሞ መለየትና ማከም የሚያስችል አቅም እየተገነባ ነው- ኢንስቲትዩቱ

ባህርዳር፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በሽታዎችን ቀድሞ መለየትና ማከም የሚያስችል የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በክልሉ የዘረመል ስነ-ህይወት ጥናትና ምርምር ማዕከል ስራ ማስጀመሪያ ስነ-ስርአት ተካሂዷል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በወቅቱ እንደገለፁት የማዕከሉ መከፈት በሽታዎችን ቀድሞ ለመከላከልና ለማከም ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው። 


 

በክልሉ የተከፈተው የዘረመል ስነ-ህይወት ጥናትና ምርምር ማዕከል በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በግሎባል ፈንድና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል ።

ይህም በክልሉም ሆነ እንደሀገር በወረርሽኝ ደረጃ ሊከሰቱ የሚችሉ አዳዲስ በሽታዎች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለመለየት፣ ለመከላከልና ለማከም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መድኃኒት የተላመዱ በሽታዎችን ለይቶ በመመርመር ክትባት እስከማምረት ሊያግዙ የሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማካሄድ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

"ይህም ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከግብርና ምርምርና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚካሄደውን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ነው" ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው የማዕከሉ መከፈት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ በሽታዎችና ወረርሽኞችን አስቀድሞ በጥናትና ምርምር ለይቶ ለማከምና መፍትሄ ለመስጠት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።

እንዲሁም መድኃኒቶች፣ ክትባቶችና የመከላከያ ዘዴዎች ውጤታማ መሆን አለመሆናቸውን በመለየት የታካሚዎችን ደህንንት ለመጠበቅ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም በሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ ማዕከላትን የማቋቋም ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶክተር ጌታቸው አስታውቀዋል።

የማዕከሉ መከፈት ዩኒቨርሲቲዎች የሚያካሂዱትን ችግር ፈቺ የጥናትና ምርምር ስራዎች ለማከናወን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ያመለከቱት ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ዋና ፀሐፊ  ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ይህም ሊከሰቱ የሚችሉና የሚከሰቱ በሽታዎች ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ፈጥኖ ለመከላከል ሁነኛ አጋዥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በማእከሉ ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና አጋሮች ተገኝተዋል፡፡    

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም