ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ጅቡቲን ጠንካራ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቅርበት መስራት ይገባል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እና ጅቡቲን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በተለያዩ መስኮች ተቀራርቦ መስራት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቴዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር) ከጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል፡፡

ሁለቱ ሚኒስትሮች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚያስችሉ የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በቅርቡ የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር አብዱልቃድር ሁሴን ኦማር የመጀመሪያ ኦፊሴላዊ ጉብኝታቸውን በኢትዮጵያ ማድረጋችው የሁለቱን ሀገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ሚኒስትር ጉዲዮን ጤሞቲዎስ(ዶ/ር) ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ጋር ያላት ግንኙነት በጉርብትና ብቻ የታጠረ ሳይሆን በፈርጀ-ብዙ ዘርፎች የተሳሰረና ስትራቴጂካዊ ዕይታ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ እና በጁቡቲ መካከል ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በቀጣናዊ ትስስር እንዲሁም በዜጎች ጉዳይ በቅርብ እየተመካከሩ መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

ሁለቱ ሚኒስትሮች በጅቡቲ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር በተያያዘ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የትራንስፖርት ኮሪደር ከማሳለጥ አኳያ የዲኪል ጋላፊ መንገድ ስራ በሚፋጠንበት ሁኔታ ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም