ቀጥታ፡

ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ስራ የሁሉንም ተሳትፎና ድጋፍ ይፈልጋል

ጂንካ፤ግንቦት 6/2017(ኢዜአ):- ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ስራ የሁሉንም ተሳትፎና ድጋፍ እንደሚጠይቅ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስገነዘበ።

የአፍሪካ አለም አቀፍ ቅርሶች ቀን ''ቅርሶች ለማህበራዊ ትስስርና ለማህበረሰብ ጥቅም'' በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ከተማ ተከብሯል።


 

በበዓሉ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ኃይሉ እንዳሉት፥ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በአፍሪካ በአለም ቅርስነት ከተመዘገቡ 147 ቅርሶች 12ቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው ።

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እና ቅርሶቹ ካላቸው ሁለንተናዊ እሴት አኳያ በድርጅቱ የተመዘገቡ ቅርሶች ውስን መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ቅርሶቹን ይበልጥ ለማስተዋወቅና አጉልቶ በማውጣት በአለም ቅርስነት እንዲመዘገቡና ዕውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ስራ የሁሉንም ተሳትፎና ድጋፍ እንደሚጠይቅም  ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል ።

በአፍሪካ ለ9ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ እየተከበረ ያለው የአፍሪካ አለም አቀፍ ቅርሶች ቀንም ለቅርሶች ትኩረት እንዲሰጥ ያግዛል ብለዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወይኒቱ መልኩ በበኩላቸው በክልሉ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ መካነ ቅርስ፣ የኮንሶ እና የጌዴኦ ውብና ማራኪ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ በአለም ቅርስነት የተዘገቡ ቅርሶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ የወላይታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ጊፋታ''በዓልን ከማይዳሰሱ የአለም ቅርሶች እንደ አንዱ ለማስመዝገብ ሂደቱ ተጠናቆ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት በመጠባበቅ ላይ ነን ብለዋል።

ከጊፋታ ቀጥሎ የጋሞ ብሔረሰብ ባህላዊ  የዳኝነትና የዕርቅ ስነስርዓት  ''ዱብሻ'' እና የመስቀል አከባበር እንዲሁም የደራሼ ብሔረሰብ  ባህላዊ የትንፋሽ  የሙዚቃ መሳሪያን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።


 

የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም አታ በበኩላቸው ቅርሶች የህዝቦችን ማንነት፣ ታሪክና ትውፊት እንዲሁም አኗኗር  የተከተበባቸው  አሻራዎች በመሆናቸው የመጠበቅና የመንከባከቡ ስራ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

በበዓሉ ላይ የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የአሪና የደቡብ ኦሞ ዞኖች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም