ቀጥታ፡

ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ልማትን ለማረጋገጥ በአርዓያነት መስራት አለብን- ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባትና ልማትን ለማረጋገጥ በአርዓያነት መስራት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በግንቦት ወር የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ የርክበ ካህናት ምልዓተ ጉባኤ ተጀምሯል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በጉባኤው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለሀገር ሰላም፣ ለዕድገቷ፣ ለአንድነትና ማህበራዊ አገልግሎት ይበልጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።

ከመቼውም በላይ የተሻለ ስራ በመስራትና ህዝብን በማገልገል ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባናል ብለዋል።

የሲኖዶሱ አባላት በማሕበራዊ አገልግሎት በመሳተፍ ሕዝበ ክርስቲያኑን ማስተማር እንደሚጠበቅባቸውም ፓትርያርኩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍም ህዝብን በማስተማር አርዓያ ሆኖ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት የኢትዮጵያ የልማትና እድገት የተሳካ እንዲሆን ሁሉም መትጋት እንዳለበት ገልጸዋል።

የግንቦት ወር የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ የስራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም