ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሩሲያ ባለሃብቶች ግንባር ቀደም ምርጫቸው ናት - አምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሩሲያ ባለሃብቶች ግንባር ቀደም ምርጫቸው መሆኗን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር) ገለጹ።

በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ሩሲያ የኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በሩሲያ 80ኛ ዓመት የድል በዓል ላይ መታደማቸውም የኢትዮ-ሩሲያን ታሪካዊ ወዳጅነት በማጠናከር የሀገራቱን ዘርፈ ብዙ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮ-ሩሲያ ግንኙነት 128 ዓመታትን አስቆጥሯል ያሉት አምባሳደር ገነት በዚህም በጤና፣ በትምህርት እና ሌሎች ማህበራዊ የትብብር መስኮች እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በስፔስ ሳይንስ፣ በጂኦ-ስፓሻል፣ በሰላማዊ የኒውክሌር ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ማዕድንና ኢንርጂ ዘርፎችም የትብብር ስምምነት በመውሰድ ጭምር በስፋት እየተሰራባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

የሩሲያ ባለሃብቶችም በአፍሪካ በሚያደርጉት የንግድና ኢንቨስትመንት ስራ ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ምርጫቸው መሆኗን ተናግረዋል።

በዚህም የሩሲያ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያሉትን የንግድና ኢንቨስትምንት ዕድሎች እንዲጠቀሙ የትብብር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የሩሲያ ባለሃብቶችም የኢትዮጵያን ቡና በቀጥታ በመግዛት በኩልም የንግድ ትብብሩ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

ሩሲያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ በየትኛውም ጊዜ ኢትዮጵያን በመደገፍ ሁነኛ ወዳጅ ሆና መቀጠሏን ገልጸዋል።

ለአብነትም እ.አ.አ. በ2024 የብሪክስ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ አባል እንድትሆን ከፍተኛ ድጋፍ ማደረጓን ጠቅሰዋል።

የብሪክስ አካል በሆነው አዲስ ልማት ባንክ(New Development Bank) ውስጥ የኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሩሲያ ገንቢ ድጋፍ ማድረጓን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም