በክልሉ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸረን ከመከላከል ባለፈ ለምርታማነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸረን ከመከላከል ባለፈ ለምርታማነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አሶሳ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ):- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸረን ከመከላከል ባለፈ ለምርታማነት መጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የግብርና ባለሙያዎች በበኩላቸው በክልሉ የተፋሰስ ልማትን በማጠናከር የህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ አስተዋጽኦ ለማበርከት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተከናወነውን የተፋሰስ ልማትና የተገኘውን ውጤት በተመለከተ ኢዜአ በክለሉ የተለያዩ አካባቢዎች ምልከታ ያደረገ ሲሆን አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮችን አነጋግሯል።
የተፋሰስ ልማት ሥራ የጠፉ ምንጮችን ከመመለስና የአካባቢን ሥነ ምህዳር ከመለወጥ ጎን ለጎን ለተቀናጀ የግብርና ሥራና ምርታማነት ማደግ አስተዋጽኦ ማድረጉን አርሶ አደሮች ይናገራሉ።
በክልሉ ኡራ ወረዳ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አርሶ አደር ሀዋ መሀመድ በክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
ሌላኛው አርሶ አደር አማረ አሰፋ፤ በተፋሰስ ልማቱ የአፈር ለምነትን በመጠበቅና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ አካባቢው በደን በመሸፈኑ ከቀርከሃና ሌሎች ችግኞች ለሽያጭና ለተለያዩ አገልግሎቶች እያዋልን ነው ብለዋል።
በተሰራው የተፋሰስ ልማት አካባቢው ከእንስሳት እንዲጠበቅ በማድረግ የተተከሉ የቀርቀሃ እና ሌሎች ችግኞችም አሁን ላይ ለሽያጭ ደርሰው ገቢ እያስገኙ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ የአቡራሞ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ፈይሰል ኑረይን፤ በአካባቢው የተከናወነው የተፋሰስ ልማት አፈር እንዳይሸረሸርና አካባቢው እንዳይራቆት አድርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
የአካባቢያቸው ትልቁ ትኩረት በዝናብ ምክንያት ተሸርሽሮ የሚወርደው አፈር ወደ ግድቡ እንዳይደርስ መከላከል መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፋንታሁን እጅጉ ናቸው።
የግብርናው ዘርፍ ሃላፊዎች ደግሞ የተፋሰስ ልማቱ ከግብርና ልማትና ምርታማነት እንዲሁም ስነ ምህዳርን ከመጠበቅ ባለፈ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ከደለል የተከላከለ መሆኑን ገልጸዋል።
የአቡራሞ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አታላይ ደረጀ፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ሁሉም ግንዛቤን አግኝቶ እንዲሳተፍ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ባበከር ሃሊፋ በክልሉ በሚገኙ ተፋሰሶች ላይ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ሰፋፊ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እየሆነና ግድቡ በደለል እንዳይሞላ አስተዋጽኦ ለማበርከት ጠንካራ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።