የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 6/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ንግድ ባንክ በ37 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ባህር ዳር ከተማ በ46 ነጥብ 3ኛ ደረጃን ይዟል።
ባህር ዳር ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በድጋሚ ወደ 8 ዝቅ ያደርጋል።
በአንጻሩ ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ከቀናው ደረጃውን ከፍ የማድረግ እድል ያገኛል።
የ29ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር በመቻል እና ስሑል ሽሬ መካከል ምሽት 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው መቻል በ40 ነጥብ 6ኛ ደረጃን ይዟል።
በአንጻሩ ውጤት የራቀው ስሑል ሽሬ በ20 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
መቻል ካሸነፈ በሊጉ ያልተሸነፈባቸውን ተከታታይ ጨዋታዎች ብዛት ወደ ስድስት ከፍ ያደርጋል።
ካለፉት ዘጠኝ ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለው ስሑል ሽሬ በዛሬው ጨዋታ ካሸነፈ ወደ ድል ጎዳና ይመለሳል።