የኢትዮጵያ የእናቶች ሞትን ምጣኔ ቅነሳ ስኬቶች እና ቀሪ የቤት ስራዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የእናቶች ሞትን ምጣኔ ቅነሳ ስኬቶች እና ቀሪ የቤት ስራዎች

የዓለም የጤና ድርጅት (ደብሊውኤችኦ) የ2025 ዓለም የጤና ቀንን እ.አ.አ አፕሪል 7, 2025 አክብሯል።
የዘንድሮው ዓመት የቀኑ መሪ ሀሳብ “ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ጥበቃ፣ ለመጻኢው ብሩህ ጊዜ” የሚል ነው።
የዓለም የጤና ጉዳዮች የበላይ አካል የሆነው ደብሊውኤችኦ መሪ ሀሳቡን መሰረተ በማድረግ ዓመቱን ሙሉ የእናቶች እና ህጻናት ጤና ጥበቃ አስመልክቶ ንቅናቄ ያደርጋል።
በኢትዮጵያም የዓለም የጤና ቀን ሚያዚያ 19 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው እንጦጦ ፓርክ “ ከቃል ያለፈ የተግባር ምላሽ” በተሰኘ ሁነት ተከብሯል።
በአከባበሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች፣ የጤና ሰራተኞች፣ ቤተሰቦች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የጤና ሚኒስቴር፣ የዓለም ጤና ድርጅት እና ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሁነቱን በጋራ አዘጋጅተውታል።
በእንጦጦ ፓርክ የነበረው የዓለም የጤና ቀን አከባበር ሁነቱን አስቦ ከመዋል ያለፈ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ ለእናቶች እና ህጻናት ሞት ቅነሳ ያላትን ቁርጠኝነት ማሳየቷን ገልጿል።
የእናቶች እና ህጻናት ጤና የጤና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ መብት፣ የማህበራዊ ልማት እና የብሔራዊ ልማት ጉዳይም ጭምር እንደሆነ የዘንድሮው የዓለም የጤና ቀን አከባበር ያሳየ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ከ100 ሺህ እናቶች መካከል ከ400 በላይ የሚሆኑት ህይወታቸውን ያጡ ነበር።
ኢትዮጵያ ይሄን አሃዝ በመቀየር የራሷን ታሪክ ፅፋለች።
በአሁኑ ሰዓት የእናቶች ሞት ምጣኔ ከ100 ሺህ እናቶች ወደ 195 ዝቅ ብሏል። ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ኢትዮጵያ በጤናው ስርዓት፣ የሰው ኃይል ስልጠና እና የአገልግሎት አቅርቦት ላይ እያደረገች ያለውን ዘላቂ ኢንቨስትመንት እንደሚያሳይ ድርጅቱ ገልጿል።
ይሁንና አሁንም በኢትዮጵያ በየአመቱ በአማካይ 8 ሺህ ገደማ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ችግር እንደሚሞቱ መረጃው ያመለክታል።
በእናቶች እና ህጻናት ጤና ጥበቃ እየተደረገው ያለው ዓመታዊ ንቅናቄ ለለውጦች እውቅና ከመስጠት ባለፈ ቀሪ የቤት ስራዎች ማጠናቀቅ እንደሚገባ የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት የሰው ኃይል ስልጠናን በማስፋት፣ የእናቶች እና ህጻናት ክብካቤን ማሻሻል፣ በዲጂታል መሳሪያዎች አማካኝነት የአገልግሎት አሰጣጥን ማጠናከር ላይ መልካም ስራዎች ቢያከናውንም አሁንም የአገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ድርጅቱ አሳስቧል።
የጤና መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ቁጥርን መጨመር ሌሎች ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው ብሏል።
የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝትና ምላሽ ስርዓትን ማጠናከር ሌላኛው በድርጅቱ የቀረበ ምክር ሀሳብ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ቤጆይ ናምቢያር በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ያለው የእናቶች እና ህጻናት ሞት አሳሳቢ እንደሆነና ጠንካራ ምላሽ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል።
በዘላቂ ልማት ግቦች እ.አ.አ በ2030 ከ100 ሺህ እናቶች የሚሞቱን ወደ 70 ዝቅ የማድረግ ግብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት ለማሳካት እየሄዱበት ያለው ርቀት አመርቂ አለመሆኑ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ከተቀመጠው ግብ አንጻር ብዙ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባት የዓለም የጤና ድርጅት አስታውቋል።
ይሁንና ኢትዮጵያ በዓለም የፋይናንስ ፈተናዎች እና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በግልጽ ያሳየች ሀገር መሆኗ ተገልጿል።
ዓለም በተግባር የታገዘ ምላሽ ከሰጠ መከላከል የሚቻሉ የእናቶች እና ህጻናትን ሞት ማስቀረት ሊሳካ የማይችል ህልም አይደለም።
ከእንጦጦ ፓርክ ጎዳናዎች አንስቶ በሀገሪቷ ክፍሎች በሚገኙ የጤና ማዕከላት የእናቶች እና ህጻናትን ሞትን ለመቀነስ የሚወሰዱ እያንዳንዱ እርምጃዎች የወደፊቱን የዓለም መጻኢ ጊዜ ብሩህ የማድረግን ራዕይን የሚያሳካ ነው ሲል የዓለም የጤና ድርጅት ጽሁፉን ቋጭቷል።