በኢትዮጵያ ያለው የሃይማኖት መከባበርና አብሮነት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ያለው የሃይማኖት መከባበርና አብሮነት ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃመድ ዓሊ የሱፍ ገለጹ።

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።


 

በጉባዔው መክፈቻ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃመድ ዓሊ የሱፍ የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ለሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት እውን መሆን የድርሻውን ይወጣል ብለዋል።

በሃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ ዓላማቸውን ሊያሳኩ የሚፈልጉ ጽንፈኞችና አሸባሪዎችን በጋራ መከላከል ከእምነት ተቋማት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑንም ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት ለሌሎች በአርአያነት የምትጠቀስ መሆኗንም አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ የሚፈለገውን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማምጣት የሃይማኖት ተቋማት የሚያደርጉትን የሰላም ውይይትና አብሮነት እንደሚደግፍም አመልክተዋል።


 

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የብሄር ነፃነትና እኩልነት እውን የሆነባት እንዲሁም አንዱ ሌላውን አክብሮ የሚኖርባት ሀገር ናት።

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተለያዩ ሃይማኖቶች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ የሚሰሩትን ተግባር እንዲያጠናክሩ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዜጎች አብሮነትና በትጋት መስራት ለዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች በትብብር መፍትሄ መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በህገ መንግስቷ ጭምር ስለ ሃይማኖቶች እኩልነት መንግስትና ሃይማኖት መለያየት በግልጽ አስቀምጣ እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።


 

በዓለም ሃይማኖት ተቋማት ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሴ ሃይሉ በዚሁ ወቅት እአአ በ2063 የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተያዘው አጀንዳ እንዲሳካ የእምነት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመሻገር የህዝቦች መከባበር፣ መተባበርና የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

የእምነት ተቋማት መልካምነትን አብሮነትና ሰላምን በመስበክ ተከታዮቻቸውን መልካም ስነ ምግባር ማላበስ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም