ቀጥታ፡

የሃይማኖት አባቶች ለህዝቦች አብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦ የሃይማኖት አባቶች ለህዝቦች አብሮነት፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አስገነዘቡ።

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባኤው ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሀመድ ዓሊ የሱፍ፣ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራን፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎችም ታድመዋል።


 

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፋት መልዕክት፤ የሃይማኖት መሪዎች ለሀገር ሰላም ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

አፍሪካ በበርካታ ተግዳሮቶች እየተፈተነች ያለች መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት በትብብርና በጋራ መፍታት ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጉላት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ እንደገለጹት፤ አሁን የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመወጣት፣ ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ወሳኝ ነው።

ሁሉም የእምነት ተቋማት ስለ ህዝቦች አብሮነት ፍቅርና ሰላም እንደሚያስተምሩ ገልጸው፤ የእምነት ተከታዮች ይህን መልካም አስተምህሮ ወደ ተግባር ሊቀይሩ ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ለህዝቦች አብሮነት ለዘላቂ ሰላምና ልማት እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በዓለም ላይ ትላልቅ ሀሳቦች ሰላምን የሚገነቡ መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ የጉባዔው ተሳታፊዎችም ተግባራዊ የሚሆን የተሻለ ሀሳብ በጋራ በማፍለቅ ለዓለም ሰላምና ፍቅር ሚናቸውን ማጉላት አለባቸው ብለዋል።

ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም ወር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገሮች የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

አለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤውን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከአፍሪካ የሃይማኖት ተቋማት ህብረት እና ከቡድን 20 የሃይማኖቶች ህብረት ፎረም እንዲሁም ከአፍሪካ ህብረት የሃይማኖቶች ፎረም ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ በአካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ጨምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ላይ በመምከር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገራት ስብሰባ ምክረ ሃሳቦች እንደሚቀርቡም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም