የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭን ስኬታማ ለማድረግ የጎላ አስተዋፅኦ ያበረክታል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭን ስኬታማ ለማድረግ የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በአፍሪካ ህብረት የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ዳይሬክተር ሃርሰን ኒያምቤ ገለፁ።

በአፍሪካውያን የሚተገበረው ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭ የባለሙያዎች እና የአጋር አካላት ስብሰባ ዛሬ በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት መካሄድ ጀምሯል።


 

በአፍሪካ ህብረት የብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ አካባቢ ዳይሬክተር ሃርሰን ኒያምቤ በዚሁ ጊዜ ለኢዜአ እንዳሉት ኢኒሼቲቩ በመላው አፍሪካ በዋናነት በሳህል ቀጣና በረሃማነትን እና የመሬት መራቆትን ለመከላከል የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው።

የረጅም ጊዜ ግብ የተጣለበት ፕሮጀክቱ ጉልህ ስኬቶችን እያስመዘገበ እንዳለም አንስተዋል።

በቀጣናው በተጀመሩ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች አርብቶ አደሮች ለከብቶቻቸው መኖ እንዲያገኙ እያስቻሉ መሆኑን ጠቅሰው፥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም አስተዋፅኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ኢኒሼቲቩ የስራ እድል በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ኢኒሼቲቭን ለማሳካት የሚያግዝ በመሆኑ ሌሎች ሀገራት ልምድ መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ መርሃ ግብሩን ወደ ሌሎች ሀገራት ለማስፋት የጀመረችውን ስራ በማድነቅ፥ ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል ነው ያሉት።


 

የአፍሪካ የደን ፎረም ዋና ፀሐፊ ፕሮፌሰር ላቦዴ ፖፑላ በበኩላቸው ኢኒሼቲቩን በታሰበው ልክ ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ሀገራት በቁጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም