ቀጥታ፡

የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ እና የቻይናዋ ሺንቺያንግ ግዛት የቢዝነስ ትብብር እና ልምድ ልውውጥ ጉባኤ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሁለቱ ሀገራት ባለሀብቶች በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢኮኖሚ በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት የላቀ ግንኙነት አላቸው።

የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መሰረተ ልማትም የሀገራቱ ግንኙነት ውጤታማነት ሌላው ማሳያ መሆኑን ገልጸው በቻይና አፍሪካ ትብብርም ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና እየተጫወተች ነው ብለዋል።

በመሰረተ ልማት፣ በአምራች፣ በግብር እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሌሎች መስኮች በሀገራቱ መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ አኳያ የቻይና ሺንቺያንግ ግዛት ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

መንግሥት ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩን ጠቁመው የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸው ለኢንቨስትመንት የተሻለ መዳረሻ እየሆነች ነው ብለዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ሀገራቱ ትብብራቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የቻይና ሺንቺያንግ ግዛት ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተሳካ ኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንዲኖራቸው በኢትዮጵያ ያለው የቻይና ኤምባሲ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።


 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢንዱስትሪ ማዕከል ለመሆን እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የግሉን ዘርፍ በኢንዱስትሪው መስክ በስፋት ለማሳተፍ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑም ጨምረው ገልጸዋል።

የቻይና ሺንቺያንግ ግዛት ባለሃብቶች በአምራች ዘርፍ እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር)፥ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተወሰዱ እርምጃዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የግሉ ዘርፍ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ የህግ ማሻሻያ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና አባል መሆኗ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ የሚያደርጋት ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም