በክልሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአፈርና ውሃ ጥበቃ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በአፈርና ውሃ ጥበቃ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

ክልሉ ለ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መረሃ -ግብር ችግኞች ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ባለፉት አመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአካባቢውን ስነ-ምህዳር መሰረት በማድረግ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።


 

በዚህም በአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ በግብርና ምርታማነትና በደን ሽፋን ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል።

በበጋ የአፈርና ውሃ ጥበቃ መረሃ-ግብር ማህብረሰቡን በማሳተፍ ሰፊ ስራ መከናወኑን ገልጸው፤ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የአረንጓዴ አሻራ ግብን ለማሳካት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

ለ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መረሃ-ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞችን እያዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የችግኝ ተከላ ቦታዎችን መለየትና ማዘመን እንዲሁም የመረጃ ተአማኒነትን ማረጋገጥ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እየተደረጉ ያሉ የችግኝ ዝግጅቶችና የተከላ ቦታዎች ልየታ በመስክ ጉብኝት ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በባለቤትነት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብሩ የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ችግኝ በማፍላት የተሠማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም