በሲዳማ ክልል 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል

ሀዋሳ ፤ግንቦት 5/2017 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አንቺንአሉ አሰፋ፤ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ኮሚሽነሯ በማብራሪያቸውም በተለይም በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ ኮንስትራክሽንና የግብርና ዘርፍ ጥሩ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 56 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አንስተዋል።

የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለወሰዱ ባለሃብቶች ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑና ለበርካቶችም የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ  በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በክልሉ ወደ ሥራ በገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ3 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

በሀዋሳ ከተማ በግብርና ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩት አቶ ቢኒያም በለጠ፤ በ800 ሺህ ብር የጀመሩት የወተት ላሞች እርባታ ሥራ አሁን ላይ ወደ 12 ሚሊዮን ብር ማደጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማዳቀል የአካባቢው አርሶ አደሮችን ያማከለ ስራ ለመስራት  እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡


 

በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ወንድወሰን ላንቃ በበኩላቸው ከውጭ የሚገቡ የሞተር ሳይክልና የመኪና መለዋወጫዎችን ጨምሮ የብረታብረት ቅርጻቅርጾችን እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስ ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን አንስተው፣ በዘርፉ መንግስት እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

በአሁኑ ወቅትም በድርጅቱ ከ30 በላይ ለሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና በቀጣይም በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀስ ሲጀምር ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።


 

በድርጅቱ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል አዲስ አለም ዘነበ፤ ከስራ እድሉ ባለፈ  ብዙዎቻችን የሙያ ክህሎታችን እያደገ ነው ብሏል።

በሀገር ውስጥ በራስ አቅም እየተመረቱ ያሉ የፋብሪካ ምርቶች ሀገርን ከውጭ ምንዛሬ ወጪ እየታደጉ መሆኑንም አንስቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም