ቀጥታ፡

ለሐጅና ኡምራ ተጓዦች ቀልጣፋና ምቹ የአየር ትራንስፖርት ለመስጠት ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ-አየር መንገዱ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለዘንድሮው የሐጅና ዑምራ ተጓዦች ቀልጣፋና ምቹ የአየር ትራንስፖርት ለመስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሐጅና ዑምራ ጉዞ ስኬታማነት በየአመቱ እያደረገ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል።

ዘንድሮ ለ1446ተኛ ጊዜ የሚደረገውን የሐጅና ዑምራ ሐይማኖታዊ ጉዞ አስመልክቶ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በዚሁ ወቅት፥አየር መንገዱ በየአመቱ ለሐጅና ዑምራ ሃይማኖታዊ ጉዞ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮም የሐጅና ዑምራ ጉዞ ስኬታ እንዲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር በማድረግ ላሳየው ቀጣይነት ያለው ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ሀላፊ ለማ ያዴቻ በበኩላቸው፥አየር መንገዱ ከኢትዮጵያና ከመላው ዓለም ወደ ሳውዲ አረቢያ ለሚጓዘው ህዝበ ሙስሊም በርካታ በረራዎችንና ሰራተኞችን በመመደብ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

ለሐጅ ተጓዞች ቀልጣፋና የላቀ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

የጉዞው ስርዓት እስኪጠናቀቅ ድረስም አየር መንገዱ አገልግሎቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዘንድሮ ለ1446ተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሐጅና ዑምራ ጉዞ ከነገ ረፋድ ጀምሮ ወደ ስፍራው የሚደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም