በኢንቨስት ኢትዮጵያ ፎረም ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚደረግ ይጠበቃል-ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኢንቨስት ኢትዮጵያ ፎረም ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚደረግ ይጠበቃል-ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦በኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ፎረም ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ 2025 ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀስላሴ በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ባለፉት ሰባት አመታት የኢንቨስትመንት ዘርፉን የሚደግፉ በርካታ የሪፎርም ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ተገማች እንዲሁም ምቹ የሆነ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ተግዳሮት የነበሩ ጉዳዮችን መቅረፍ መቻሉን ገልጸዋል።
በኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ፎረም ሶስት ጉዳዮችን ማሳካት የሚፈልግ መሆኑን የገለጹት የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሩ፥የመጀመሪያው በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያሉ መልካም እድሎችን ማስተዋወቅ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑን ኢትዮጵያ ለዘርፉ እድገት የሚያግዙ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ማሻሻያዎችን ማሳወቅ ከፎረሙ የሚጠበቅ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁለተኛው አዳዲስ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳየት መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ለኢንቨስትመንት የተመቸች ሀገር መሆኗን ግንዛቤ የሚፈጥር ፎረም መሆኑን ገልጸዋል።
ተጨባጭ የሆነ የኢንቨስትመንት ስምምነት ከፎረሙ በሶስተኛነት የሚጠበቅ ውጤት መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህ አንጻር ባለፉት ወራት ሲሰራባቸው በቆዩ ፕሮጀክቶች ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኢንቨስትመንት ስምምነት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣በገንዘብ ሚኒስቴር እና በአጋር የልማት ድርጅቶች አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው ኢንቨስት ኢትዮጵያ 2025 ፎረም በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።