በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት ያላቸውን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው-ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በአህጉሪቱ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት ያላቸውን ሚና የበለጠ ማጠናከር አለባቸው-ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የእምነት ተቋማት ያላቸውን ሚና የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
3ኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ ዓሊ የሱፍ፣ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮች፣ ምሁራን፣መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና ሌሎችም ታድመዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባስተላለፋት መልዕክት የሃይማኖት መሪዎች ለአገር የሰላም ግንባታ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የሃይማኖት አባቶች ያላቸውን የማይተካ ሚና የበለጠ ማጉላት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
እርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመወጣትና ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የጀመረችው አገራዊ ምክክር ውጤታማ እንዲሆን የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን አንስተው ሚናቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሃመድ ዓሊ የሱፍ በበኩላቸው፥ የአፍሪካ ህብረት የG-20 አባል እንደመሆኑ ለሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት በትኩረት በመስራት አፍሪካ ሰላምና ልማቷ እውን የሆነ አህጉር ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት ለሌሎች ምሳሌ የምትሆን አገር መሆኗንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በወቅቱ፥ ኢትዮጵያ የሃይማኖትና የብሄር ነፃነትና እኩልነት የተረጋገጠባት እንዲሁም አንዱ ሌላውን አክብሮ የሚኖርባት አገር መሆኗን አንስተዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተለያዩ ሃይማኖቶች ለአገር ሰላምና ልማት በጋራ እንዲሰሩና በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የትኛውም ሃይማኖት ለሰላም ለዜጎች አብሮነትና ለልማት በትጋት መስራትና ለአለምአቀፍ ተግዳሮቶች በትብብር መፍትሄ መስጠት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።
በጉባኤው በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ፣ በአካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ጨምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ላይ በመምከር ለቡድን 20 አባል አገራት ምክረ ሃሳብ እንደሚቀርብም አንስተዋል።
በአለም ሃይማኖት ተቋማት ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር አምባሳደር ሙሴ ሃይሉ በዚሁ ግዜ እአአ በ2063 የበለፀገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የተያዘው አጀንዳ እንዲሳካ የእምነት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አለምአቀፍ ተግዳሮቶች ለመሻገር የህዝቦች መከባበር፣ መተባበርና የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የእምነት ተቋማት መልካምነትን አብሮነትና ሰላምን በመስበክ ተከታዮቻቸውን መልካም ስነ ምግባር ማላበስ አለባቸው ብለዋል።
በኢኮኖሚ የተሳሰረችና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ የሃይማኖቶችን እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ እንደሚገባው አንስተው ፤ በዚህ ላይ የሃይማኖት ተቋማት በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም ወር በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
አለምአቀፍ ጉባኤውን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአፍሪካ የሃይማኖት ተቋማት ህብረት እና ከቡድን 20 የሃይማኖቶች ህብረት ፎረም ከአፍሪካ ህብረት የሃይማኖቶች ውይይት ፎረም ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁትም ተነግሯል።