የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትብብርና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትብብርና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ትብብርና ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ዘላቂ ደህንነት በትብብር አበክራ እንደምትሰራም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀጣናዊ መረጃና ደህንነት ኮሚቴ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ኢትዮጵያ ለአብሮነትና ለአካባቢያዊ ሰላም ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፤ የትኛውም ሀገር ጎረቤቶቹ በስጋት ውስጥ ሆነው ብቻውን ሊበለፅግ አይችልም የሚል ፅኑ አቋም እንዳላትም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ከማስጠበቅ ባለፈ በሌሎች ሀገራት ችግር ሲከሰት ሰላም በማስከበር እንዲሁም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካ መር መፍትሔን በማራመድ መጓዟንም ጠቅሰዋል።
አፍሪካ የተኩስ ድምፅ የማይሰማባትና ሰላማዊት አህጉር እንዲሁም ምስራቅ አፍሪካን የተረጋጋ ቀጣና የማድረግ ራዕይ ሊሳካ የሚችለው በትብብር፣ የጋራ ዓላማና በተግባር ቁርጠኝነት መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣናው አሁንም በፈተናዎች ውስጥ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የሽብር ቡድን እንቅስቃሴዎች፣ ፅንፈኝነትና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ትርምስ የሚፈጥሩበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለቀጣናው ሰላም ትልቅ ስጋት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው አንዱ ሀገር በሌላው ሀገር ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ድጋፍ በማድረግ የሚፈጥራቸው የውክልና ግጭቶች ናቸው ብለዋል።
የውክልና ግጭቶች ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንደሚያስከትሉ አይተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ተቋማትን በመቦርቦር የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሲያውኩ፣ የስርዓት አልበኝነት መገለጫ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አንስተዋል።
የውክልና ግጭትና መሰል ችግሮችን በጊዜ መቀልበስ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንንም በጋራ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚገባ አንስተዋል።
ሀገራት በትብብር ኦፕሬሽን ሲፈጽሙና መረጃ ሲለዋወጡ የወንጀለኛ ቡድኖችን የትስስር መረብን በመበጣጠስ ማዳከምና የዜጎችን ህይወት መታደግ እንደሚችሉ በተግባር መታየቱንም ጠቅሰዋል።
ሽብርተኝነትን በጋራ መዋጋት፣ የኮንትሮባንድ መስመሮችን መዝጋት፣ ወንጀልን የሚደግፉ የገንዘብ ምንጮችን ማድረቅ የግድ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በጋራ ስንቆም የበለጠ ስኬትን ማረጋገጥ እንችላለን ብለዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ሦስት ተልዕኮዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አንስተዋል።
የመጀመሪያው ሀገራት የራሳቸውን የውስጥ ደህንነት በራስ አቅም መቆጣጠር እንጂ ከሌላ የውጭ አካል መጠበቅ እንደሌለባቸው ተናግረዋል።
ሁለተኛው ጉዳይ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር መሆኑን ገልጸው፥ የመረጃና ደህንነት ተቋማት በየጊዜው መወያየት፣ መተባበር፣ መተማመንና የጋራ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት።
ሌላኛው ጠንካራ ተቋማትን መገንባት መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም የዘመኑን የደህንነት ስጋቶች በአግባቡ መቀልበስ የሚችሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና በብቁ ሙያተኞች የተደራጁ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ መድረክም ተግዳሮቶችን በመለየት በጋራ ለመፍታት ቁርጠኝነት የምንወስድበት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ጠንካራ እና ይበልጥ የተዋሃደ ቀጣና ለመፍጠር ዝግጁነቷን በማንሳት፥ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በስብሰባው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ 13 ሀገራት የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኃላፊዎች፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ናቸው።