ክልሎቹ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በአይነትና በብዛት የችግኝ ዝግጅት እያደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ክልሎቹ ለዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በአይነትና በብዛት የችግኝ ዝግጅት እያደረጉ ነው

አዳማ፤ግንቦት 5/2017 (ኢዜአ)፦ለዘንድሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር በአይነትና በብዛት የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አስታወቁ።
በሁለቱ ክልሎች ለዘንደሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር የሚመለከታቸውን የስራ ሃላፊዎች አነጋግሯል።
በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ በዚህ ዓመት በክልሉ ቡናና ሻይ ቅጠል፣ፍራፍሬን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው በ420 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ከችግኝ ዝግጅቱ በተጓዳኝ የተከላ ቦታ ልየታ፣የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች ቁፋሮ እና ሌሎችም አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አመላክተዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ኸሊፋ፤ በክልሉ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 75 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ መያዙን ጠቅሰው፥ በዚህም መሰረት በአይነትና በብዛት ችግኞችን በማፍላት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በእስካሁኑ ሂደትም ችግኞች የሚተከሉትን ቦታ የመለየትና ማዘጋጀት እንዲሁም የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚተከሉት ችግኞች ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ሃላፊዎቹ አስረድተዋል።