የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራሁ ነው- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ ለመሆን እየሰራሁ ነው- የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ግንቦት 5/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ገለጸ።
በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የምርት ጥራትና ደህንነት መጠበቅ ሲቻል መሆኑን ተከትሎ ኢትዮጵያም ለምርት ጥራትና ደህንነት መረጋገጥ ትኩረት ሰጥታ በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
ለዚህ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን የግብርና ግብዓት፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርትና አገልግሎት ጥራት እንዲሁም ደህንነትን ለማረጋገጥ ተቋቁሟል፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ በእንስሳት ምርትና ግብዓት ጥራት ጉድለት ሊመጡ የሚችሉ የጤና ችግሮችን መከላከል የሚያስችል የቁጥጥር ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ጀማል ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ባለስልጣኑ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የእንስሳት ምርት ደረጃዎችን በማስከበር በምርት ጥራትና ደህንነት ጉድለት በሰዎችና በእንስሳት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ችግር የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የግብርና ግብዓትና ምርት የሚያመርቱ ተቋማትን መመዝገብና ብቃታቸውን ማረጋገጥ፣ ገቢና ወጪ ምርቶችን በተቀመጠው የጥራትና ደህንነት መስፈርት ማረጋገጥ እንዲሁም ለወጪ ምርቶች የጥራት ሰርቲፍኬት መስጠት ተቋሙ በዋናነት የሚሰራቸው ተግባራት መሆኑን አብራርተዋል።
የእንስሳት ምርት ጥራትና ደህንነትን በመጠበቅ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ከዘርፉ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ 95 ከመቶ የሚሆነው የእንስሳት መድኃኒት ከውጭ እንደሚገባ ገልጸው፥በዚህ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውና የጥራት ደረጃቸውን ያላሟሉ መድኃኒቶች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ መደረጉን አክለዋል፡፡
በባለስልጣኑ የአዳማ ጣቢያ ኃላፊ ዶክተር ለማ ምንዳ ወደ ውጭ የሚላኩ እንስሳትን ጤንነት የሚከታተሉባቸው አምስት ማቆያና ማደለቢያ ስፍራዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በእነዚህ ማቆያዎች የእንስሳቱን ጤንነት የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በቄራው የስጋ ጤንነት መርማሪና ተቆጣጣሪ ዶክተር ደምረው ኪዳነ ማሪያም በበኩላቸው፥በዓለም አቀፍ ገበያ ጤናማ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የቁጥጥር ስራው ወሳኝ ነው ብለዋል።
በዚህም የስጋውን ጤንነት ካረጋገጡ በኋላ ወደ ውጭ መላክ የሚያስችል ማረጋገጫ እየሰጡ ስለመሆናቸው ገልጸዋል።
ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጠ ስጋ ለደንበኞቻችን እንድናቀርብ ባለስልጣኑ ፈቃድ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፍና ክትትል እያደረገልን ይገኛል ያሉት ደግሞ በቄራው የሲስተም ማናጀር የሆኑት አቶ አርቀው በላይነህ ናቸው።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በአራት ማዕከላት ፣በዘጠኝ ቴክኒካል ዲፓርትመንቶች እና በ45 ጣቢያዎች አማካኝነት ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡