የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በመጠቀም እየተከናወኑ ባሉ አገልግሎቶች የተገኙ ስኬቶችን በጥናት አስደግፎ ማሳየት ያስፈልጋል- ኮሚሽነር ሙኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በመጠቀም እየተከናወኑ ባሉ አገልግሎቶች የተገኙ ስኬቶችን በጥናት አስደግፎ ማሳየት ያስፈልጋል- ኮሚሽነር ሙኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፡-የዲጂታል ቴክኖሎጂ አገልግሎትን በመጠቀም እየተከናወኑ ባሉ የህዝብ አገልግሎቶች የመጡ ስኬቶችን በጥናት አስደግፎ ማሳየት እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ "ፐብሊክ ሴክተር ትራንስፎርሜሽን ኤንድ ዴቬሎፕመንት' በሚል ርዕስ 10ኛውን የምርምር ጉባኤ እያካሄደ ይገኛል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት የመጡት ስኬቶችን በጥናት ማሳየት ተገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት ለህዝብ አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታል መሰረተ ልማት በፍጥነት እየተዘረጋ መሆኑን አመልክተው፤ ሆኖም የዲጂታል ትራስፎርሜሽን ስኬቶች የሚመዘገቡት በቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ሳይሆን ሰውን ማዕከል ያደረገ፣ የተቋማትን ዝግጁነትና የፖሊሲ ማዕቀፍ ጭምር ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ ጥናቶች የሚሰሩትን ከማይሰሩት በመፈተሽ እንዴትና ለምን በሚል መጠየቅ ውጤት በማምጣት አቅጣጫ ማሳየት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
በሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም ተግባራዊ ተደርገው በዜጎች ዕለታዊ ህይወት ላይ ያመጡትን ውጤቶች የሚዳስሱ ጥናቶችም አስፈላጊ መሆናቸውን ነው ያመለከቱት።
መልካም አስተዳደር ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን ያመለከቱት ኮሚሽነር ዶክተር ሙኩሪያ ፤ ለዚህም ጥናቶች አቅጣጫ የሚያመለክቱ በመሆን የጉዟችን ወሳኝ አካል ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ንጉሱ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤በአገሪቷ በሁሉም ዘርፎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን እየተመዘገበ ቢሆንም ያሉትን ውስብስብ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ሳይንሳዊና ችግር ፈቺ ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተመረጡ ተቋማት ተግባራዊ ለተደረገው አዲሱ የሲቪል ሰርቪስ ፖሊሲ ሪፎርም ውጤታማነት በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
የጥናትና ምርምር ስራዎችን ውጤታማነት ለማሻሻል፣ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ተመራማሪዎችን በስፋት ለማፍራት እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፉን ብቃት ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮተቤ የትምህርት ዩንቨርስቲ መምህር እስከዳር ግዛት በበኩላቸው፥ በተቋማት ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ምርምሮች ተወዳዳሪነት እንዲሁም የሲቪል አገልግሎት ሰጪውን ብቃት በማጎልበት በኩል ያላቸውን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የምርምር ጉባኤው ለፖሊሲ አውጪዎችም ግብዓት ከማሰባሰብ አኳያ የሚኖረውን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፍርዲሳ ጀቢሳ (ዶ/ር) የአገሪቱን ውስን ሀብት ተጠቅመው የሚከናወኑ ምርምሮች ችግር ፈቺና ለማህበረሰቡ ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።
የመንግስት አስተዳደርና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የከተማ ልማትና አሰተዳደር ላይ ያተኮሩ 33 ጥናቶች በጉባኤው እንደሚቀርቡም ተመልክቷል።