ኮሚሽኑ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ማስፈን ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ይሰራል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ማስፈን ዋንኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ ይሰራል- መሐሙድ አሊ ዩሱፍ

አዲስ አበባ፤ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ አስተዳደር በአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ማስፈን ዋንኛ የፖሊሲ የትኩረት አቅጣጫው በማድረግ እንደሚሰራ የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ሊቀ-መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ ከሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር ዛሬ ትውውቅ እና ቆይታ አድርገዋል።
ሊቀ-መንበሩ በስልጣን ጊዜያቸው ሊያሳኳቸው ስላቀዷቸው ተቋማዊ ግቦችና ቅድሚያ ሰጥተው ለመፈጸም ያሳቧቸውን ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ገለጻ አድርገዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ አስተዳደር በሰላም፣ ደህንነት፣ ልማትና ዓለም አቀፍ ትብብር ላይ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
መሐመድ አሊ ዩሱፍ ሰላምና ደህንነት የኮሚሽኑ ዋንኛ የትኩረት ማዕከል መሆኑን አመልክተዋል።
ኢ-ሕገ መንግስታዊ የመንግስት ለውጦች በአፍሪካ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀናቸውን ተናግረዋል።
የአፍሪካ ህብረት መሰል ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም ሰላምን በማስፈንና የዴሞክራሲ ስርዓትን በማረጋገጥ የህብረቱ አባል ሀገራትን ሉዓላዊነት እና ደህንነት መጠበቅ ላይ አበክሮ ይሰራል ነው ያሉት።
ሊቀ-መንበሩ በገለጻቸው ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ መድረክ የአፍሪካን ድምጽ የበለጠ ለማጉላት እንደሚሻ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ የአፍሪካ ህብረትን ሚና ማጠናከር ቁልፍ ግብ መሆኑን ጠቅሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግበት በጽኑ ሁኔታ እንደሚሟገት አመልክተዋል።
ሊቀ-መንበሩ የፀጥታው ምክር ቤት አሁናዊ መዋቅር የታሪክ ኢ-ፍትሃዊነት በማለት የገለጹት ሲሆን አፍሪካ በዓለም አስተዳደር የሚገባትን ትክክለኛ ስፍራ በሚገልጽ ሁኔታ ምክር ቤቱ ማሻሻያ ሊደርግበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በዲጂታል ኢኮኖሚና ሰው ሰራሽ አስተውሎት አማካኝነት በአፍሪካ ፈጠራ እና ዘላቂ ልማትን ማሳለጥ ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው ብለዋል።
የህብረቱ ኮሚሽን ከቀጣናዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ በማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ወጥነት ባለው መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሊቀ-መንበሩ በአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል አማካኝነት ወረርሽኝን የመከላከል ዝግጁነት እና ምላሽ አቅም ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱንም አንስተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ሊቀ-መንበር መሐመድ አሊ ዩሱፍ በቀጣይ ከሀገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጋር በየሶስት ወር ጊዜ ቆይታ እንደሚያደርጉ ለማወቅ ተችሏል።
በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ መሐመድ አሊ ዩሱፍ ሙሳ ፋቂ ማህማትን በመተካት የኮሚሽኑ ሊቀ-መንበር ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።