ኢትዮጵያ የጂኦፓርኮቿን እና ጂኦ ቱሪዝም ቦታዎችን አልምታ ለመጠቀም በትኩረት እየሰራች ነው -ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጂኦፓርኮቿን እና ጂኦ ቱሪዝም ቦታዎችን አልምታ ለመጠቀም በትኩረት እየሰራች ነው -ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የጂኦፓርኮቿ እና ጂኦ ቱሪዝም ቦታዎችን አልምታ ለመጠቀም በትኩረት እየሰራች መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ገለፁ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት ጋር "የዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ጂኦፓርኮች እና ጂኦቱሪዝም ለዘላቂ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ አውደጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሸን እና የኢትዮጵያ ላይዘን ቢሮ ኃላፊ ሪታ ቢሶኖውት (ዶ/ር) ጨምሮ የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች፣በዘርፉ የተሰማሩ የኢትዮጵያዊያን እና የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
አውደ ጥናቱ በዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክስ እና ጂኦቱሪዝም ላይ ያሉ ባለድርሻ አካላትን አቅም ማሳደግ ጨምሮ የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ማስጀመር እና የጂኦፓርክ ጽንሰ ሃሳብን በአህጉሪቱ ማስተዋወቅ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው አምስት የኢኮኖሚ አውታሮች አንዱ ቱሪዝም ነው።
በዚህም ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል ለሀገር እድገት እንዲያበረክት ተደርጎ እየተመራ እንዳለ አንስተው፥ይህም የተሰጠውን ትኩረት ለማዳበር እና ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ፈጥሯል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በጂኦ ፓርኮችን እና በጂኦቱሪዝም ትልቅ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሯ፥ሀብቶቹን የማስመዝገብና ተፍጥሯዊ ይዘታቸውን የመጠበቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም ቦታዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመልካ ቁንጡሬ መልከአምድርን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የዩኔስኮ የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሸን እና የኢትዮጵያ ላይዘን ቢሮ ኃላፊ ሪታ ቢሶኖውት (ዶ/ር) አፍሪካ ሁለት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ጆኦ ፓርኮች እንዳላት ተናግረዋል።
እነዚህም በታንዛኒያ እና ሞሮ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም በርካታ የጂኦቅርሶች ያላት ሀገር ናት ብለዋል።
እነዚህን ቦታዎች በማስተዋወቅ ለመጠቀም እያደረገች ላለው ሂደት ዩኔስኮ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
ዘርፉን በተመለከተ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂዮሎጂ መምህር ፕሮፌሰር አስፋወሰን አስራት በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በርካታ የጂኦፓርኮችን እና ጂኦ ቱሪዝም ስፍራዎች እንዳለት ገልፀው፥ እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ ለመጠቀም ግንዛቤ ላይ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
በታንዛኒያ የንጎሮንጎ ሌንጋይ የዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ አስተባባሪ አግነስ ጊዲና (ዶ/ር) የንጎሮንጎ ሌንጋይ የጆፓርክ ስፍራ ከአፍሪካ በዩኔስኮ ግሎባል ጂኦፓርክ ከተመዘገቡ ቦታዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ቦታው በዩኔስኮ መመዝገቡ አካባቢውን በዓለም ደረጃ በማስተዋወቅ በርካታ ቱሪስቶች እንዲጎበኙት ማስቻሉንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ የጂኦፓርኮች ያሏት ሀገር በመሆኗ አካባቢዎችን ማልማት ላይ መስራት እንዳለባት ጠቅሰዋል።
የጂኦፓርክ ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ትኩረት መስራት እንደሚገባ የተናገረው ደግሞ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ነው።
ቦታዎችን ለመለየትና ለማስመዝገብ የተጀመረው እንቅስቃሴ በዘርፉ አበረታች ውጤት ለማምጣት የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሷል።