የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ህዝብን ከማገልገል ባለፈ በደም ለገሳም እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ህዝብን ከማገልገል ባለፈ በደም ለገሳም እየተሳተፉ ነው

ድሬደዋ፣ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ የድል ጮራ ሆስፒታል የጤና ባለሙያዎች ለህብረተሰብ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ከመስጠት በዘለለ ህይወት ለመታደግ ዛሬ ደም ለግሰዋል።
ዛሬ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ተገኝተው ደም የለገሱት ከአስተዳደሩ ከሁሉም የመንግስት ጤና ተቋማት የተወጣጡ የጤና ባለሙያዎች መሆናቸውም ታውቋል።
የጤና ባለሙያዎቹ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በሙያቸው ህብረተሰቡን በማገልገል ጤናማና አምራች ዜጋ የመፍጠር ተልዕኳቸውን ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው።
የጤና መኮንን ቢያልፈው ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በሙያቸው ህሙማንን ከመታደግ ባለፈ በበጎ ፍቃደኝነት ደም በተደጋጋሚ በመለገስ ህይወትን ለመታደግ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው።
በወሊድ ወቅት እናቶችና ህፃናት በደም እጦት እንዳይቸገሩ ለማስቻል የእኛም ደም መሠረታዊ ሚና ይጫወታል'' ብለዋል።
ሌላኛው የጤና ባለሙያ ክሊኒካል ነርስ አብዮት አስራት በበኩላቸው፥ በገጠርና በከተማ የምንገኝ የጤና ባለሙያዎች ያስተማረንን ህብረተሰብ ጤና ለመጠበቅ በትኩረት እየሰራን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በደም እጥረት ህይወት እንዳይጠፋ ደም እየለገስን እንገኛለን" ያሉት የጤና ባለሙያው፤ ጤናማና አምራች ዜጋ የመፍጠርን ተልዕኮ ለማሳካት ሌት ተቀን እየተጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ደም በመለገስ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ፤ በአስተዳደሩ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ህብረተሰቡን በቁርጠኝነት እያገለገሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጤና ባለሙያዎች ይህንን ተልዕኮ ለማሳካት ኃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ከመወጣት በተጨማሪ ደማቸውን በመለገስ ለህብረተሰቡ አለኝታ መሆናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ ላደረጉት በጎ ተግባርም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።