ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል - አምባሳደር ጁንግ ካንግ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል - አምባሳደር ጁንግ ካንግ

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦ ኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን ጠንካራ ትብብር የበለጠ ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ገለጹ።
የኮሪያ ሪፐብሊክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባለፈ መስዋዕትነት የተከፈለበትና በደም የተገመደ ጭምር ነው፡፡
በዚህም የኮሪያ ሪፐብሊክ እና የኢትዮጵያ ግንኙነት 74 ዓመታትን አስቆጥሮ ዛሬ ላይ የደረሰ ሲሆን በጦርነቱ ኢትዮጵያ የነበራት ተሳትፎ ኮሪያ ሪፐብሊክ አሁን ላይ ለተጎናጸፈችው ነፃነት ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡
በተለይ ባለፉት 20 ዓመታት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ሁለቱ ሀገራት በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ጠንካራ ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል።
ኢትዮጵያ ለኮሪያ ሪፐብሊክ ነጻነት የከፈለችው መስዋዕትነት የኮሪያ ሪፐብሊክ ህዝብና መንግስት ሁል ጊዜም እውቅና የሚሰጠውና ምስጋና የሚቸረው ታሪክ ነው ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ያለችውን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ሁሉን አቀፍ ትብብር ለማጠናከር በጋራ ፍላጎት ላይ ተመስርተው እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለአብነትም በባህል ልውውጥ፣ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤናና መሰረተ ልማት ግንባታ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በተጨማሪም በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍም እንዲሁ ያላቸውን ትብብር በማጎልበት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ረገድ የምታደርገው ጠንካራ ተሳትፎ የሚደነቅ እና ክብር የሚሰጠው መሆኑንም አምባሳደሩ አክለዋል።
74ኛ ዓመቱን ያስቆጠረውን የኮሪያ ሪፐብሊክ ሰላም ማስከበር ተልዕኮን ጨምሮ ኢትዮጵያ በኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ሱዳን፣ ሱማሊያ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ያከናወነችው የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተጠቃሽ ነው።
ኢትዮጰያና ኮሪያ ሪፐብሊክ ዘመናትን የተሻገረና በመስዕዋትነት የተሳሰረ ወዳጅነት እንዲመሰርቱ አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል ነው ያሉት።