ቱሪዝሟ እያደገ የመጣው፣በባህላዊ ምግቦቿ እና ቡናዋ ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸራት ኢትዮጵያ

በባህላዊ ታሪኳ እና ልዩ በሆኑ የምግብ አዘገጃጀቶች የምትታወቀው ኢትዮጵያ የበለጠ የዓለምን ትኩረት  እየሳበች ትገኛለች።

የናይጄሪያው ቢዝነስ ደይ ጋዜጣ ጋዜጠኛ ቺሶም ማይክል በጋዜጣው ላይ  ባሰፈረው ጽሁፍ ብዙዎች በአፍሪካ ምርጡ ምግብ እና በዓለም ላይ ምርጡ ቡና ብለው የሚናገርላት ሀገር ብትሆንም አገሪቷ አሁንም ከሌሎች የአህጉሪቱ መዳረሻዎች ጋር ስትነጻጸር በአንፃራዊነት ጥቂት ቱሪስቶችን የምታስተናግድ ሀገር  እንደሆነች ይገልጻል።

ሞሮኮ እ.አ.አ በ2024 17 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቱሪስቶችን ስትቀበል ኬንያ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ጎብኚዎችን አስተናግዳለች።

ኢትዮጵያም የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ የመሆን ጊዜዋ እየመጣ ይመስላል።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (ዩኤንደብሊውቲኦ) በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት እንዳመለከተው እስከ 2024 ባለው አምስት ዓመት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አለም አቀፍ ቱሪስቶች በ40 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

54ቱንም የአፍሪካ ሀገራት የጎበኙ አንድ ተጓዥ ኢትዮጵያን ሁለተኛ የቱሪዝም ተመራጭ አድርገውታል።

"ለዚች ሀገር በጣም የተለየ ነገር ነው ያለኝ ብዙ ጥሩ የተፈጥሮ ቦታዎች አሏት" ብሏል።

ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ቱሪዝምን የኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ አካል ለማድረግ ያሳየው ቁርጠኝነት እንደሆነ ጋዜጠኛው ይገልጻል።

በዩቲዩብ ላይ ከ5 ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያለው  የቱሪዝም ይዘት ላይ ድሪው ቢንስኪ ይህንኑ ሀሳብ ይጋራል።

“ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ምርጥ ምግብ አላት። እንጀራ በጣም ጣፋጭ ነው በዓለም ሌላ ቦታ እንደዚህ ያለ ምግብ የለም። በአፍሪካ ምርጥ ምግብ፣ በዓለም ምርጥ ቡና ያለው እዚህ ሀገር ነው።”

"እንጀራ ከጤፍ የተሰራ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ምግብ ውስጥ በጣም ዋና አካል ነው። እንጀራው ከብዙ ምግቦች እና ቅመሞች ጋር ይቀርባል።" ሲል ገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁት በምግብ እና ቡና ብቻ አይደለም። ቱሪስቶች በኢትዮጵያ የተፈጥሮ እና ታሪካዊ መዳረሻዎች በጣም ይማረካሉ። በድንጋይ ከተቀረጹ የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት በጣም የሚጎበኙ የቱሪዝም መስህብ ነው። በጥልቅ ስምጥ ሸለቆ የታጀበው የሰሜን ተራሮች ለሰዎች ምቹ የእረፍት ጊዜ የሚሰጡ ናቸው።

መዲናዋ አዲስ አበባ የባህል እና የምግብ ሁነቶች ማዕከል ናት።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት አካሄድ ቅርስ፣ መልክዐ ምድሮች እና ባህላዊ ልምዶችን ጨምሮ የተለያዩ መዳረሻዎችን ማስተዋወቅ ላይ ያተኮረ ነው።

ካላት የቱሪዝም መዳረሻ አንጻር በኢትዮጵያ ብዙ ጎብኚዎች ባይኖሩም  ያሏትን እድሎች በማስተዋወቅ ተደራሽነቷን እያሰፋች ነው።

ልዩ ማንነት ያለው እና ጥልቅ ታሪክ ያላትን ኢትዮጵያን መጎብኘት ለሚሹ ሰፊ የቱሪዝም እድሎችን የምታቀርብ ሀገር ናት ይላል ጋዜጠኛው።

በኢትዮጵያ ቱሪዝም እየጨመረ  ብዙ ጎብኚዎች በምግቧ፣ ቡናዋ እና ታሪካዊ መዳረሻዎቿ እየተሳቡ ነው።

በኢትዮጵያ ባህል እና የምግብ አሰራር ከዕለት ተዕለት የዜጎች ህይወት የተቆራኘባት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ የተለየ ነገር ማቅረቧን ቀጥላለች። የቱሪዝም ሀብቶቿ ገና ያልተነካ ነው ኢትዮጵያ የወደፊት የዘርፉ እድገት አቅም ትልቅ ነው በማለት ጋዜጠኛ ቺሶም ጽሁፉን ቋጭቷል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም