ቀጥታ፡

ስፖርት ከውድድር ባለፈ የህዝቦችን ትስስርና አንድነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው- ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ

ባምባሲ፤ ግንቦት 3/2017 (ኢዜአ)፡-ስፖርት ከውድድር ባለፈ የህዝቦችን ትስስርና አንድነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ ተናገሩ።

6ኛው መላው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውድድር ዛሬ በባምባሲ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።


 

በውድድሩ 15 ወረዳዎች በ11 የስፖርት አይነቶች የሚሳተፉ ሲሆን ውድድሩም እስከ ግንቦት 14 ቀን 2017 ድረስ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ነፊሳ አልማሃዲ እንደተናገሩት ስፖርት ከውድድር ባለፈ የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስርና አንድነትን ለማጠናከር ያግዛል።

የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር በሁሉም አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ ውድድሩ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልና የስፖርት ዓይነቶች አካቶ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ለኦሎምፒክ እና ለመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር ተሳታፊ ስፖርተኞችን ለመለየት እና የስፖርቱን ልማት ለማስፋፋት ያግዛል ነው ያሉት።

መንግስት ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ተሳታፊ የሚሆንበትና ህዝባዊ መሰረት ያለው የስፖርት ፖሊሲ በመቅረጽ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢብራሂም መንሱር በበኩላቸው ከዚህ በፊት በተካሄዱ የመላው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጨዋታዎች ውድድር ክልሉ በርካታ ስፖርተኞችን ሲያፈራ እንደነበር አስታውሰዋል።

እንደሀገር ተቋርጦ የቆየው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ውድድር ዳግም እንዲካሄድ መወሰኑ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እና ለሁሉም ስፖርቶች የተሰጠውን ትኩረት ለማየት መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ብለዋል።

"ክልሉ ከሀገር ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ስፖርተኞችን ያፈራ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ለስፖርት ልማት ትኩረት በመስጠት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ተወዳዳሪዎችም በቆይታቸው ስፖርታዊ ጨዋነትን በመላበስ ውድድሩን እንዲያካሂዱ አስገንዝብዋል።

በዕለቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ መለሰ ኪዊ እንዲሁም የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም