መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በመስዋዕትነት እያስጠበቀ የሚገኝ አኩሪ ሰራዊት ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በመስዋዕትነት እያስጠበቀ የሚገኝ አኩሪ ሰራዊት ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በመስዋዕትነት እያስጠበቀ የሚገኝ አኩሪ ሰራዊት ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
የምዕራብ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በነቀምቴ ስታዲየም እየተከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሰረት፣ ከፍተኛ ጄነራል መኮንኖችና ሌሎች አመራር አባላት ተሳትፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እንዲሁም የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ እና የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊት ውድ ህይወቱን በመስጠት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት እያስጠበቀ የሚገኝ አኩሪ የህዝብ ልጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ጠላቶች በሁለም አቅጣጫ እየመከተ የሀገርን አንድነት አስጠብቆ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲከናወኑ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ምዕራብ ዕዝ በየግዜው ጀግኖችን እያፈራ ያለ የሰራዊቱ ክፍል ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለወገን መከታ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዕዙ ከሌሎች ዕዞች ጋር በመሆን ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ሌት ተቀን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ጋሻ ሆኖ በሁሉም አቅጣጫ ጀግንነትን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለምዕራብ ዕዝ የሰራዊት አባላት 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።