ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ይጠናቀቃል 

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦  የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ የ26ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።

የሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ከአዳማ ከተማ ጋር ይጫወታል።

ንግድ ባንክ በ25ኛ ሳምንት ቦሌ ክፍለ ከተማን 5 ለ 0 በማሸነፍ አንድ ጨዋታ እየቀረው የሊጉ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል።

ቡድኑ የሊጉ አሸናፊ የሆነው በውድድር ዓመቱ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ መሆኑ በሊጉ ያለውን የበላይነት ያመለክታል።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሊጉን ዋንጫ ሲያነሳ በተከታታይ ለአምስተኛ ጊዜ በአጠቃላይ ደግሞ ለስምንተኛ ጊዜ ነው።

በሌላኛው የ26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ከመርሃ ግብሮቹ መጠናቀቅ በኋላ ንግድ ባንክ ዋንጫውን ይረከባል። 

በሊጉ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም