የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3 /2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ40 ነጥብ 6ኛ ስፍራን ይዟል። አዳማ ከተማ በ23 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ካሸነፈ በሊጉ አራተኛ ተከታታይ ድሉን ያስመዝግባል።
ባለፉት ስምንት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ያላሸነፈው አዳማ ከተማ ማሸነፍ ወደ ድል እንዲመለስ ያደርገዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ ቡና በ45 ነጥብ 3ኛ፣ ወላይታ ድቻ በ41 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዘዋል።
የ29ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።
ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ54 ነጥብ እየመራ ነው። ባህር ዳር ከተማ በ46 ነጥብ ይከተላል።
መቀሌ 70 እንደርታ ፣ አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛሉ።
የሃዋሳ ከተማው ዓሊ ሱሌይማን በ12 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ነው። የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በ11 ግቦች ይከተላል።
የኢትዮጵያ መድኑ መሐመድ አበራ፣ የመቻሉ ሽመልስ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ እና የፋሲል ከነማው ጌታነህ ከበደ በተመሳሳይ 10 ጎሎችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።