ቀጥታ፡

ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 3/2017(ኢዜአ)፦ ቦትስዋና ግብርና እና ቱሪዝምን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ያላትን የሁለትዮሽ ትስስር ለማጠናከር እንደምትሻ ምክትል ሚሲዮን መሪ ፖፒ ማምቢ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የቦትስዋና ፕሬዝዳንት ዱማ ቦኮ ከወራት በፊት የሀገራቱን ትብብር ማጠናከር ያለመ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገው ነበር።

በኢትዮጵያ የቦትስዋና ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ፖፒ ማምቢ ቦትስዋና እና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለ ብዙ ወገን ማዕቀፍ በተለያዩ መስኮች ጥሩ የሚባል ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይሁንና ሀገራቱ ትብብራቸውን በኢኮኖሚ፣ ባህል እና የህዝብ-ለህዝብ ትስስርን የበለጠ ማጠናከር የሚችሉበት ምቹ እድሎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ እያደገ እንዲመጣ ትፈልጋለች ብለዋል።

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በየካቲት ወር 2017 ዓ.ም በህብረቱ ዋና መቀመጫ በአዲስ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

ፖፒ ማምቢ የቦትስዋናው ፕሬዝዳንት ዱማ ቦኮ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ሀገራቱ ንግድ፣ ልማት እና ቀጣናዊ ሰላምን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በወቅቱ በነበረው ውይይት በሁለቱም ወገን በኩል የሀገራቱን ትስስር የበለጠ ለማጎልበት ከፍተኛ ቁርጠኝነት መታየቱን አመልክተዋል።

ቦትስዋና እና ኢትዮጵያ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ቁልፍ መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነቶች ለመፈራረም የመጨረሻው ደረጃ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት ምክትል ሚሲዮን መሪዋ።

ይህም የግንኙነት ማጠናከሪያ እድሎችን ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ቦትስዋና ከኢትዮጵያ ጋር ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ፋርማሲዩቲካል እና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ትብብሯን የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቦትስዋና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1999 ነው።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ መከባበር እና በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ይገለጻል።

ቦትስዋና በአዲስ አበባ ኤምባሲ ያላት ሲሆን ኢትዮጵያም ፕሪቶሪያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ከቦትስዋና ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን እያከናወነች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም