ኢዜማ በእውቀት ላይ ለተመሰረተ እና ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መጎልበት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል-ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜማ በእውቀት ላይ ለተመሰረተ እና ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መጎልበት ሚናውን አጠናክሮ ይቀጥላል-ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በእውቀት ላይ ለተመሰረተ እና ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መጎልበት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ /ኢዜማ/ የአመራር ማሰልጠኛ 'ኢዜማ አካዳሚ' አስመርቋል።ፓርቲው የተመሰረተበትን ስድስተኛ ዓመትም አክብሯል።
በመድረኩ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፣የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባላት እና የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አባላት ተገኝተዋል።
የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአመራር አካዳሚው በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የፖለቲካ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚችሉ ብቃትና ስነ ምግባርን የተላበሱ ተተኪ የፖለቲካ አመራር አባላትን ለማፍራት ያለመ ነው።
በአሁኑ ወቅት የዓለም የፖለቲካ ሁኔታ በብዙ መቀየሩን ገልጸው፤ አካዳሚው በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ባህል ለመገንባት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።
በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ ፖለቲካ አገርን ወደፊት ለማስኬድ እንደማያስችል አስገንዝበዋል።
አገርን እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ፖለቲካ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፥ኢዜማ በእውቀት ላይ ለተመሰረተ እና ለሰለጠነ የፖለቲካ ባህል መጎልበት ሚናውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ እና የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ሊቀ መንበር አብዱልቃደር አደም (ዶ/ር) የፖለቲካ ፓርቲዎች የትምህርት አካዳሚ መክፈት በተለያዩ አገሮች የተለመደ አሰራር መሆኑን አንስተዋል።
ኢዜማ ይህንን የአመራር አካዳሚ ለመገንባት የወሰደው ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ከተገኙት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት መካከል የአብን ሥራ አስፈጻሚ አባል ዩሱፍ ኢብራሂም እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ጸሀፊ ደስታ ዲንቃ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
አካዳሚው በእውቀት የተመራ ፖለቲካ እንዲኖር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
ፓለቲካችን በሀሳብ የበላይነት መሆን አለበት ያሉት አመራር አባላቱ አካዳሚው የእውቀት ምንጭ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
አካዳሚው በውስጡ የመማሪያ እና የሰልጣኞቹ ማደሪ ክፍሎች እንዲሁም ቤተ መጻህፍትን በውስጡ አካቷል።