ሆስፒታሉ ፈጣንና ቀልጣፋ የሕክምና አገልግሎት እየሰጠን ነው

ሀዋሳ፤ግንቦት 2/2017 (ኢዜአ)፦የሀዋሳ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ፈጣንና ቀልጣፋ በመሆኑ ሳይጉላሉ ህክምና እያገኙ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተገልጋዮች ተናገሩ።

በሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ከወረቀት ነጻ በማድረግ የተጀመረው አሰራር የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ ማስቻሉን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል።

በሀዋሳ አዳሬ አጠቃላይ ሆስፒታል በተመላላሽና ተኝቶ ህክምና ክፍል ህክምና ሲከታተሉ አግኝቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው ታካሚዎች እንደገለጹት የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ እጅግ እየተሻሻለ መጥቷል።

በሀዋሳ ከተማ ዱሜ ቀበሌ ለህክምና የመጣችው ወጣት ኬራዊ ብሩ እንዳለችው፥ በሆስፒታሉ የተገልጋይ ብዛት ከፍተኛ ቢሆንም አገልግሎት አሰጣጡ ፈጣንና ቀልጣፋ ነው።

ሌላው አስተያየት ሰጪና በተመላላሽ ህክምና ክፍል ላቦራቶሪ የደም ናሙና ሲሰጥ ያገኘነው ወጣት አበበ ደገፋው እንዳለው፥ የሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ በጣም እየተሻሻለ መጥቷል።

አገልግሎት አሰጣጣቸው የሙያ ስነ-ምግባሩን በተከተለ መንገድ እያስተናገዱን ስለሆነ ይህ አሰራር በዚህ መልኩ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በሆስፒታሉ ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ ያሉት ወይዘሮ አባይነሽ አበበ በበኩላቸው፥ የአስም ህመማቸው ተነስቶ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጡ መተንፈስ አቅቷቸው ራሳቸውን ስተው እንደነበረና በሀኪሞቹ በተሰጣቸው ህክምና እንደተሻላቸው ገልጸዋል።

የሆስፒታሉ ሀኪሞችም በተገቢው መንገድ ተቀበለው እያከሟቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በሆስፒታሉ የድንገተኛ ህክምና ክፍል ጠቅላላ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ዘመድኩን ማሙሻ፤ በሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት በርካታ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር የሆስፒታሉ ተገልጋዮችም አገልግሎቱን በአግባቡ እየተጠቀሙበትና እርካታም እንዳለው መናገር ይቻላል ብለዋል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘነበ ቱልጨ እንዳሉት፥ በሆስፒታሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ከወረቀት ነጻ በመሆኑ አገልግሎቱ ቀልጣፋ እንዲሆን አስችሎታል።

አገልግሎት አሰጣጡ ተገልጋይን ከእንግልት ነጻ እንዲሆን የሚያስችል ሲስተም መዘርጋቱና በየሶስት ወሩ ተገልጋይ ቅሬታውን የሚገልጽበት የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ቅሬታዎችን በፍጥነት መፍታት እንዳስቻለም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም