የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት ችግርን እየቀረፉ፤ምቹ አገልግሎትም እየሰጡ ነው- የመዲናዋ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት ችግርን እየቀረፉ፤ምቹ አገልግሎትም እየሰጡ ነው- የመዲናዋ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በቅርቡ አገልግሎት የጀመሩ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት እንግልትን ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመንግስትና የግል አጋርነት የመዲናዋን ነዋሪዎች የትራንስፖርት ችግር የሚቀርፉ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን በቅርቡ ስራ ማስጀመራቸው ይታወቃል።
የኤሌክትሪክ አውቶቡሶቹ የጉዞ ቲኬት ክፍያን ጨምሮ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓትን በማካተት ከአየር ብክለት የጸዱ፣ ፈጣን፣ ዘመናዊና በርካታ ሰዎችን በምቾት የሚያጓጉዙ ናቸው።
የመዲናዋ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ አዳዲሶቹ አውቶብሶች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚፈጠረውን የትራንስፖርት መጨናነቅ በማቃለል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይግኛሉ።
ከተገልጋዮቹ መካከል አድነው ብርሃኑ፥ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሰቀሱት ዘመናዊ አውቶብሶች የትራንስፖርት ችግርን በማቃለል ምቾትና ጥራት ያለው አገልግሎት እየሰጡን ነው ብሏል።
የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ በተመጣጣኝ የገንዘብ ክፍያ ምቾት ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡን ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ኤልሳ ካሳሁን ናት።
እንደ ታሪኩ ይማም ገለፃም፥ የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ ወደስራ መግባት በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚፈጠረውን የትራንስፖርት እጥረት እየቀረፉ ናቸው።
ከአውቶብሶቹ ካፒቴኖች መካከል ምንይችል ጌትነት፥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ተገልጋዮችን በፍጥነትና ምቾት በማስተናገድ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ ነው ብለዋል።
ተሽከርካሪዎቹ በተመጣጣኝ ዋጋ የመዲናዋን ነዋሪዎች በተሻለ ፍጥነት አገልግሎት እየሰጡ ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ካፒቴን ዘቢደር ባዩ ናት።
ካፒቴን ውብአዲስ ደሳለኝ በበኩሉ፥ አውቶብሶቹ አስተማማኝ የቴክኒክ ደህንነት እንዳላቸው ገልጾ፥ ነዋሪዎች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚያጋጥማቸውን የትራንስፖርት መጨናነቅ በመቀነስ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግሯል።
የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ያብባል አዲስ፥የነዋሪዎችን የትራንስፖርት ችግር ማቃለል የሚያስችሉ ተጨማሪ 100 የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ወደስራ ገብተዋል ብለዋል።
የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ የትራንስፖርት ችግር በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ስምሪት በመስጠት ለነዋሪዎች ፈጣንና ምቹ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የመዲናዋን ነዋሪዎች የትራንስፖርት አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ ተቋማትና ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።