ምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል - ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦ ምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በማስከበር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪ እና የተኩስ አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ ገለጹ፡፡
የምዕራብ ዕዝ የተመሰረተበትን 47ኛ ዓመት ምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት "የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ገድሎች " በሚል ርዕሰ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም አማካሪና የተኩስ አመራር አመራር ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ፤ የምዕራብ ዕዝ የተሰጡትን ግዳጆች በብቃት የሚወጣ የጀግኖች መፍለቂያ ነው ብለዋል፡፡
የምዕራብ ዕዝ የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጸና እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ካደረጉት የሰራዊቱ ዕዞች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ዕዙ ኢትዮጵያን ያኮራና በርካታ ጀግኖችን ያፈራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተሰጡትን ግዳጆች በብቃት በመወጣት የአገር አለኝታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ሸኔ እና ጽንፈኛ ቡድኖች ሰላምን ለማወክ ያደረጉትን ጥረት በማክሸፍ ሰላም እንዲሰፍን ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ አስፋው ቀኖ በበኩላቸው፤ "የሰላምና የልማት ሰራዊት እና ህዝብ ትስስር " በሚል ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ እንዳመለከቱት፤ በኢትዮጵያ ልማት እንዲስፋፋ ሰላምን በማስፈን በኩል ሰራዊቱ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ለውጊያ ድጋፍ አገልግሎት ሜጀር ጄኔራል ሙላት ጀልዱ በዚሁ ወቅት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የምዕራብ ዕዝ የምስረታ 47ኛ በዓል መከበር የዕዙን ታሪክ ለመሰነድና ለትውልድ ለማሻገር ነው ብለዋል፡፡
ምዕራብ ዕዝ ለሰራዊቱ አለኝታ ከሆኑ አንጋፋና ታሪክ ሰሪ ዕዞች መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሠለ መሰረት፣ ከፍተኛ ጄኔራል መኮንኖችና ሌሎች አመራር አባላት ተሳትፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
በዕለቱም የፎቶ አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን፤ ዕዙን በተመለከተ የተዘጋጀ መጽሐፍ እና ዘጋቢ ፊልም እንዲሁም የምዕራብ ዕዝ ሎጎ ተመርቋል።