እየተከናወኑ የሚገኙ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ለሥርዓተ ምህዳር መጠበቅ ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ

አዳማ፤ግንብት 2/2017 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ለሥርዓተ ምህዳር መጠበቅ እና ለምርትና ምርታማነት መጨመር ወሳኝ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማስፈፀሚያ የአምስት ዓመት ማእቀፍ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም እንዳሉት፥በኢትዮጵያ እየተካሄዱ የሚገኙ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ለሥርዓተ ምህዳር መጠበቅና ለምርትና ምርታማነት መጨመር ወሳኝ ናቸው።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት አረንጓዴ አሻራ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ እንደ ሀገር ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ከተተከሉት ውስጥ ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚገመቱት የደን ችግኞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይም ለዓለማችንና ለሀገራችን ዋና ተግዳሮት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥና የመሬት መራቆት ችግርን ለመቀልበስ የአረንጓዴ አሻራና የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ አዋጅ ተደንግጓል ብለዋል።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት ያላትን ከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አስታውቀዋል።

የአረንጓዴ አሻራና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ሀገራችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገባችውን የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦችን፣የተራቆቱ መሬቶች ማገገሚያ ጊዜን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

የቀጠናው ልማት የተመሰረተው በእኛ ውሀ ነው ያሉት አቶ ከበደ፥ የውሀው መሰረት ደግሞ ደኖቻችን ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም በመንግሥት የተዘጋጀው የአረንጓዴ አሻራና የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ድንበር ተሻጋሪ አሻራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የአረንጓዴ አሻራና የተጎዱ መሬቶች ማገገሚያ ፕሮግራም ማዕቀፍ አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን ጌቱ፥ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ሠነድ እንዳመላከቱት ልዩ ፈንዱ ለአረንጓዴ አሻራ ስራዎች ቋሚና ተቋማዊ ሥርዓት ያለው የፋይናንስ አቅም እንዲኖር ለማስቻል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም የአየር ንብረት ለውጥን በዘላቂነት የሚቋቋም እና ከአየር ንብረት ብክለት የፀዳ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተያዘውን አገራዊ ራዕይ ለማሳካት የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም በማድረግ፣የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደኖችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለአገራችን ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና የሥነ ምህዳር ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ ወሳኝ መሆኑንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም