የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል ልናዳብር ይገባል - የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ - ኢዜአ አማርኛ
የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ባህል ልናዳብር ይገባል - የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ
አዲስ አበባ፤ግንቦት 2/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የሀሳብ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲያዊ ባህል ልናዳብር ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ገለጹ።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከዚህ ቀደም የመጣንበት የመገፋፋት የፖለቲካ ባህል እንደ ሀገር ወደፊት እንዳንጓዝ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት።
ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል ያሉት ሰብሳቢው፥ መጠፋፋቱንም፣ማውደሙንም አይተናል፤ ምንም የተጠቀምነው ነገር የለም ሲሉም ነው የተናገሩት።
ሰው ማሸነፍ ያለበት በሀሳብ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ የኃሳብ ልዕልና መከበር እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ መልካም እሴቶችን በማጎልበት የዴሞክራሲ ሽግግሩ ውጤታማ እንዲሆን የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑንም አብራርተዋል።
ፓርቲዎችም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሀገርና ሕዝብን ማስቀደም ይጠበቅባቸዋል፤ምሁራንም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሀገሩን የሚወድ ውይይትንና ሠላማዊ የፖለቲካ አካሄድን ያስቀድማል ያሉት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ፤ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት በር መክፈት ይገባል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት የተጀመረው ጥረት መልካም የሚባሉ ውጤቶችን እንደሚያመጣ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ትርክቱን ለመገንባት የሚረዱ ጉዳዮች ላይ በትኩረት መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
አንድ የሚያደርጉ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ሥራው ውጤታማ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን አሻራ ሊያኖሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የውይይት ባህል እንዲዳብር የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማካሄድ ለአገር ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ እየተሰራ ነው።
በተለይም የምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ምን ዓይነት ገንቢ ሚናዎችን መጫወት እንደሚችሉና ቅንጅታቸውን ይበልጥ በማጠናከር ለዴሞክራሲ ባህል መዳበር የጎላ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
በአገር ደረጃ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ምክር ቤቱ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አጀንዳ እያቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።