በምስራቅ ቦረና ዞን ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል በ99 ተፋሰሶች የልማት ስራ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ቦረና ዞን ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል በ99 ተፋሰሶች የልማት ስራ ተከናውኗል

ነጌሌ ቦረና፤ግንቦት 2/2017 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ቦረና ዞን ድርቅና የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል የሚያስችል 99 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የተፋስስ ልማት ስራ መከናወኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በተፋሰስ ልማት ስራው ከ188 ሺህ በላይ የዞኑ ህዝብ መሳተፉ የተገለጸ ሲሆን ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ የግጦሽ መሬት ከንክኪ መከለሉም ተገልጿል።
በጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ቡድን መሪ አቶ አልይ አረባ፣ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው በዋናነት በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚያጋጥመውን ድርቅና የአካባቢ መራቆት መከላከልን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በበጋ ወራት በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች 63 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያካልል የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
የተፋሰስ ልማት ስራው የማሳና የተራራ ላይ እርከን፣ የተለያዩ የውኃ አካላትንና ምንጭ ማጎልበት እንዲሁም ችግኝ ዝግጅትን ያካተተ እንደነበረ ገልጸዋል።
በዚህም 99 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ በተከናወነ ስራ ከ188 ሺህ በላይ ህዝብ መሳተፉን ገልጸው፥ ከችግኝ ዝግጅት ባለፈ 500 ሺህ የችግኝ መትከያ ጉድጓዶች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ለበጋ ወራት አገልግሎት የሚሰጡ 12 የተለያዩ የውሀ አካላትን የማዘጋጀት ስራም የዚሁ አካል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
በተፋሰስ ልማት ስራው 10 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ የግጦሽ መሬት ለመከለል ታቅዶ ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከንክኪ መከለሉንም አንስተዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች በአመዛኙ በአርብቶ አደርነት ህይወታቸውን እንደሚመሩ ገልጸው፥ የተከለለው የግጦሽ ሳር መሬት ከ60 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።