ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ ነው -የክልሎች እና ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፦መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ በቋሚነት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን የተለያዩ ክልል እና የከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የተለያዩ ክልል እና የከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ግልጽና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የታጠቀ ነው።

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግስት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀላጥፍና ከህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ኮከቤ ዲዳ በዚሁ ወቅት፤ መሶብ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከመሶብ ያገኙትን ልምድ በኦሮሚያ ክልልም ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ ይህም የተገልጋይን እንግልት በመቀነስ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማቀላጠፍ ያስችላል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን እንዳሉትም፤ መሶብ ባለጉዳዮች ወደ ተለያዩ ተቋማት የሚያደርጉትን ምልልስ የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሶብ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂን አቀናጅቶ የያዘ ትልቅ ተቋም መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ በተቀላጠፈ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርግ መሆኑንን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ገብሬ ጋጌ በበኩላቸው፥ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መንግሥት ለዜጎች ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት ለመሥጠት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከከተማዋ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሚያስፈልጉ አዋጆች፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን መጽደቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አሰፋ ጉራቻ በበኩላቸው ዛሬ ያገኙትን ልምድና ተሞክሮ በክልላቸው ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የቦታ መረጣ ስራዎች መከናወን መጀመራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፋራህ አብዲላሂ በበኩላቸው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በክልሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመር ምርጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ነው።

በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 የፌደራል መንግስት ተቋማት ተቀናጅተው ከ41 በላይ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም