ቀጥታ፡

ባለፉት የለውጥ አመታት ሀገራዊ የዲጂታል ግብይትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ምቹ መደላድል ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ አመታት ሀገራዊ የዲጂታል ግብይትን ይበልጥ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ምቹ መደላድል ተፈጥሯል ሲሉ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ፡፡

ኢትዮ-ቴሌኮም በአይነቱ እና በተደራሽነቱ የተለየ "ዘመን ገበያ" የተሰኘ የዲጂታል ግብይት ፕላት ፎርም ይፋ አድርጓል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮ-ቴሌኮም የቴሌኮም እና የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ፈር ቀዳጅነቱን አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ቴሌ ብርን ጨምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ስራ ላይ በማዋል ከግብይት ተደራሽነት እና ከፋይናንስ አካታችነት አንጻር አመርቂ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ኩባንያው በኢትዮጵያ ልማት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ ሚና ያላቸውን ዘርፎች ለይቶ በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል፡፡

ባለፉት የለውጥ አመታት የዲጂታል ግብይትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ምቹ መደላድል መፈጠሩን ነው የተናገሩት፡፡

ይፋ የተደረገው "ዘመን ገበያ" ዲጂታል ፕላት ፎርም እስካሁን የነበረውን የዲጂታል ግብይት ስርዓት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ገልጸዋል።

ተገበያዮች በአካል መገናኘት ሳይጠበቅባቸው ግብይቾቻቸውን በኦንላይን እንዲፈጽሙ የሚያስችል እና አላስፈላጊ ወጪን የሚያስቀር መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

"ዘመን ገበያ" የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሸጋገር አዎንታዊ ሚና እየተወጣ መሆኑን ጠቁመው ከአነስተኛ እስከ ትልልቅ የንግድ ድርጅቶችን በማገናኘት የገበያ ተደራሽነትን የሚያሰፋ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በስራ እድል ፈጠራ፣ በምርታማነትና በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍም እንዲሁ፡፡

ፕላት ፎርሙን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል የቴክኖሎጂ እና የኢንተርኔት መሰረተ ልማቶች መሟላታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የግብይት ፕላት ፎርሙን አስተማማኝነት በሚመለከታቸው አካላት ተረጋግጦ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም