የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መሰማራታቸው ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ትልቅ ጠቀሜታ አለው - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን - ኢዜአ አማርኛ
የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መሰማራታቸው ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ትልቅ ጠቀሜታ አለው - አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፦ የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መሰማራታቸው ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚያዊ ትብብር ዕድገት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።
የሩሲያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ አቅም በመረዳት በኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በግብርና ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውንም ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጊኒ ተረክሂን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን ለኢኮኖሚ ልማት እና ለዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚጠቅም ገልጸዋል፡፡
ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገርም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግንኙነት መድረክ ያላትን ታሪካዊ ሚና የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በሀገሮቻችን መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር መሠረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የሚገኙ የሩሲያ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን የገበያ አቅም በመረዳት በኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በግብርና ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት መሳየታቸውንም ተናግረዋል፡፡
ይህም በቅርብ ጊዜ ውስጥ እውን እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ፤ በሩሲያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እና ሩሲያ መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመው፤ በ2024 የመጀመሪያዎቹ 10 ወራት በሀገራቱ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ በ40 በመቶ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ የንግድ ውክልና በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያሉትን ዕድሎች ለመፈተሽ ከሚፈልጉ ኩባንያዎች ጥያቄዎችን እየተቀበለ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በአውቶሞቲቭ ማምረቻ፣ በኢነርጂ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ቁሳቁስ፣ በኬሚካል ምርቶች፣ በምግብ ማቀነባበሪያ፣ የፋርማሲዩቲካል ዘርፍ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተያዘው ዓመትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ መሰማራት ለሚፈልጉ የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች ሰፊ ዕድሎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቦሌ ለሚ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሃዋሳ፣ ጅማ፣ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ሌሎችም የኢኮኖሚ ዞኖች መኖራቸው ለሁለትዮሽ ትብብሩ ዕድገት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የሩሲያ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ መሰማራት ለሁለትዮሽ የኢኮኖሚያዊ ትብብር ዕድገት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
እነዚህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እንደ የተሳለጠ የአንድ-ማዕከል ሂደት፣ የታክስ እና የጉምሩክ ማበረታቻዎች እንዲሁም አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ያሟሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡