የኢትዮጵያ መድን እና የባህር ዳር ከተማ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መድን እና የባህር ዳር ከተማ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች 16ቱን ሲያሸንፍ በ3ቱ ሽንፈት አስተናግዶ በ6 ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
34 ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ግቦችን አስተናግዶ በ54 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው 25 ጨዋታዎች 12ቱን ሲያሸንፍ በ6ቱ ተሸንፎ በ7ቱ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ 30 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 14 ግቦችን አስተናግዶ በ43 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በአንጻሩ ባህር ዳር ከተማ ማሸነፍ ከቻለ ደረጃውን ወደ ሁለተኛ ከፍ እንዲያደርግ እና ከመሪው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት እንዲያጠብ ያስችለዋል።
በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ሁለቱ ክለቦች የሚያደርጉት ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሚያዚያ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በከተማው በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ዛሬ በሃዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ እንዲደረግ የሊጉ የውድድር እና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ መወሰኑ የሚታወስ ነው።