የአዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታና ነባሮችን የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
የአዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታና ነባሮችን የማሻሻል ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 1/2017(ኢዜአ)፦ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ የአዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ፣ የነባሮች ማሻሻያና ማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ ገለጹ።
ዋና ዳይሬክተሩ ለኢዜአ እንደገለጹት የአየር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 23 አውሮፕላን ማረፊያዎች መደበኛ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም 22 የአነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎች በባለስልጣኑ እውቅና አግኝተው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
በፌደራል መንግስት አምስት ኤርፖርቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቅሰው፥ ነባሮቹ ላይም የማስፋፊያና የማሻሻያ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ካላት የቆዳ ስፋት፣ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም የትራንስፖርት ፍላጎት አንጻር ያለው መሰረተ ልማት በቂ አለመሆኑን ገልጸው፥ የሀገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ከፌዴራል መንግስት በተጨማሪ የክልል መንግስታት፣ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ባለሀብቶች ኤርፖርት እንዲገነቡ እና እንዲያስተዳድሩ የሚያስችል መመሪያ ማውጣቱንም ገልጸዋል።
በዚሁ መሰረት 32 አዳዲስ አነስተኛ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ለመገንባት ጥያቄ መቅረቡን በመጠቆም ባለስልጣኑ ቦታው ድረስ በመሄድ መረጣ ማካሄዱን አስገንዝበዋል።
ወደ ግንባታ የገቡ፣ በጥናት ላይ የሚገኙ እና ፋይናንስ ማፈላለግ ላይ የሚገኙ መኖራቸውንም ነው ያነሱት።
በቱሪዝም መዳረሻ አካባቢዎች፣ በቀላሉ የሚበላሹ የግብርና ምርቶች እና ማዕድናት ባሉባቸው አካባቢዎች እንደሚገነቡ ገልጸው ለዚህም በብሔራዊ የኤርፖርቶች ልማት መሪ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።