ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሀገራዊ ጥረቶች እንዲሳኩ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሀገራዊ ጥረቶች እንዲሳኩ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ሀገራዊ ጥረቶች እንዲሳኩ የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የትብብርና የቅንጅት መድረክን በተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የፌዴራል ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ግንባታ እና ግጭት አፈታት፣ በዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም በአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ድርጅቶቹ ሚናቸውን በላቀ ደረጃ እንዲወጡ መንግሥት በርካታ የሪፎርም ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል።
በተለይም ህጎችና አዋጆችን በማሻሻል ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሻለ መንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎችም ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ነው ያነሱት።
ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱም አስቸኳይ ድጋፎችን በማስተባበርና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ተጠቃሽ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ጠቁመው፤ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸው ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሀገር ግንባታ ሂደትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድርሻ የላቀ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸው ጥረቶች እንዲሳኩ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ ይገባል ብለዋል።
መንግሥት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ ተግባራዊ ያደረጋቸው የለውጥ ሥራዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጫወቱት ገንቢ ሚና ከፍ እንዲል ማድረጉን አብራርተዋል።
ድርጅቶች እና መንግሥት በጋራ የሚሰሩበት መሰል የትብብር መድረክ መፈጠሩ በቀጣይ የተሻለ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ሁሴን፤ የቅንጅትና የትብብር መድረኩ ከፌዴራል እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ አደረጃጀት ያለው መሆኑን አንስተዋል።
መድረኩ በዐቢይና ንዑስ ኮሚቴ የሚመራ ሲሆን፤ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ የሚገጥሟቸውን ችግሮች አቅርበው መፍትሄ የሚበጅበት ነው ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በኢትዮጵያ የካቶሊክ ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ አቶ ዘመዴ አበበ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በመንግሥት መካከል ወጥ የሆነ ቅንጅታዊ ሥርዓት መዘርጋቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ማህበረሰቡን በአግባቡ ለማገልገል ዕድል ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል።
የብሄራዊ ማህበራዊ ተጠያቂነት ህብረት ዋና ሥራ አስኪያጅ መኩሪያው ጫኔ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በራስ አቅም ችግሮችን የመቋቋም አቅም ለመፍጠር ማህበረሰቡን ለአንድ ዓላማ ማሰባሰብ፣ ግንዛቤውንም የማሳደግ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ማህበራት ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚሰሩ ስራዎች ላይ ከዚህ ቀደም ሲሳተፍ ቆይቷል፤ አሁንም ገንቢ ሚናውን ይገፋበታል ብለዋል።