ቀጥታ፡

ስታርታፖች የፈጠራ ውጤቶቻቸውን በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሙከራ ደረጃ መተግበር ሊጀምሩ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ ስታርታፖች የፈጠራ ውጤቶቻቸውን በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሙከራ ደረጃ በቅርቡ መተግበር የሚችሉበት አሰራር መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የመጀመሪያው የመንግስት እና የግል ተቋማት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ትብብር መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)ና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ተቋሙ በስሩ የሚገኙ የልማት ድርጅቶችን ለማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየሰራ ነው።

ስታርታፖችንና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለመደገፍ ከተቋማት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

ለዚህም በተቋሙ ስር ባሉ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የስታርታፖች የፈጠራ ውጤቶች በሙከራ ደረጃ እንዲተገበሩ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባ ተናግረዋል።



የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ኢትዮጵያን ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ እመርታ እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለሁሉም በሚል መርህ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፣ የመሰረተ ልማትና የቴክኖሎጂ ልማት ላይ እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወጣቶችና ስታርታፖች እንደገለጹት፥ ኢንስቲትዩቱ የስልጠናና የተለያዩ የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገላቸው ይገኛል።


 

የአሴር ቴክኖሎጂ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዘሩባቤል ደረሰ፥ በግብርና እና ስፔስ ሳይንስ ላይ በአርቲፊሻል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስራ የሚሰራ ስታርታፕ እንዳለው ገልጿል።

በዘርፉ ያለውን እውቀት ለማበልፀግ የሚረዳ ስልጠና ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት መከታተሉን ጠቅሶ፥ መንግስት የጀመራቸውን የድጋፍ ኢኒሼቲቮችም አድንቋል።

በጡት ካንሰር ልየታ ላይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ ስራ እየሰራች መሆኗን የገለፀችው ቃልኪዳን ከበደ፥ ኢንስቲትዩቱ ከስልጠና ባለፈ የቴክኒክ ድጋፍ እንዳደረገላት ተናግራለች።

የትብብር መድረኩ በኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ምህዳር ውስጥ የመንግስት እና የግል ዘርፉን ትብብር እና ፈጠራ ለማጎልበት ያለመ ሲሆን፤ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውጤት የሆኑ የቴክኖሎጂ ምርቶች ለዕይታ ቀርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም