በማህበራቱ እየተከናወነ ያለው ሪፎርም ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ያልተገባ ውድድርን ማስተካከል የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማህበራቱ እየተከናወነ ያለው ሪፎርም ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ያልተገባ ውድድርን ማስተካከል የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ በሚገኙ የኀብረት ስራ ማህበራት እየተከናወነ ያለው ሪፎርም ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ያልተገባ ውድድርን ማስተካከል የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ ገለፁ።
አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትን የሪፎርም የሥራ ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸውም በቦሌ፣ በየካ፣ በልደታና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትን ተመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኀብረት ስራ ማህበራት የተረጋጋ ኢኮኖሚ በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው።
በዚህም ኮሚሽኑ ማህበራቱ በሚጠበቅባቸው ልክ መስራት እንዲችሉ የሪፎርም ስራ እየተከናወነ እንዳለ ገልፀዋል።
ነባር ማህበራትን ዳግም በማደራጀት ለህዝቡ ተገማችና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማድረግን ያለመ ነው ብለዋል።
ይህም የማኅበራቱን አቅም በማጎልበት እና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ነው ያስረዱት።
ከዚህ አንፃር የሪፎርም ስራው ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ያልተገባ ውድድርን ማስተካከል በሚያስችል መልኩ እየተከናወነ እንዳለ ለመመልከት መቻላቸውን ነው የተናገሩት።
የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ማህበራቱ ያላቸውን የእርስ በእርስ ትስስር ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዚህም ሂደት የአስተዳደሩ አመራሮች ጨምሮ የዘርፉ አመራሮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽነር ልእልት ግደይ ማህበራቱ ጥራት ያለው፣ ፍታሃዊና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ ሪፎርም እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ይህም ማህበራቱ የአዲስ አበባን እድገት በሚመጥን መልኩ የማደራጀት እና ዘመናዊ አስራርን ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየተሰራ እንዳለ ተናግረዋል።