ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በዞኖቹ የማህበራዊ ልማት ሥራዎችን በማከናወን የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን እየሞላ ነው

ጂንካ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአሪ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ከፈጥኖ ደራሽ ሥራዎች ባሻገር የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን እየሞላ መሆኑ ተገለጸ።

ዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን በጂንካ ከተማ ተከብሯል።

በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኦሞ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ቢሻው ለኢዜአ እንደገለጹት ማህበሩ በሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት እየሰራ ይገኛል።

በዚህም ከፈጥኖ ደራሽ ሥራዎች ባሻገር በሌሎች የልማት ሥራዎችም የሚጠበቅበትን ማህበራዊ ሃላፊነት ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ለዚህም ማህበሩ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በአሪ ዞን እና በደቡብ ኦሞ ዞን የማህበረሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላት ያከናወናቸውን ተግባራት በማሳያነት ጠቅሰዋል ።


 

በመድረኩ የተገኙት የአሪ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ እና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የቦርድ አባል አቶ ይኼነው ተስፋዬ በበኩላቸው ማህበሩ የመንግስትን የልማት ክፍተቶችን በመሙላት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ባለው ጥረት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበሩ በዞኑ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል እንዲጎለብት ለትውልድ አርአያ የሚሆን ተግባር እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።


 

የጂንካ ነዋሪ አቶ አህመድ ሙሐመድ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ባህል እንዲጎለብት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

ማህበሩ በማህበራዊ ልማት መስክ ሚናውን እየተወጣ ያለ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው፣ ማህበሩ ይህን መልካም ተግባሩን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ማህበሩ ከመንግሥት ጋር በመተባበር እያደረገ ላለው ድጋፍ ቀጣይነት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

''ሰብአዊነትን እናፅና!'' በሚል መሪ ሐሳብ የዓለም ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ቀን ለ67ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት ተከብሯል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም