ቀጥታ፡

በክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር)

ሚዛን አማን፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሰረተ ልማቶችን በማሳደግና ለአምራቾች ድጋፍ በማድረግ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) ተናገሩ።

የክልሉ ሦስተኛ ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ ተካሂዷል።


 

በንቅናቄው ላይ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር) እንዳሉት፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የኢንዱስትሪን የማምረት አቅም በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ያስፈልጋል።

መንግስት በሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቅሰው፣ በክልሉም በኢኮኖሚ ዘርፍ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ትኩረት መደረጉን ገልጽዋል።

በክልሉ 750 የሚጠጉ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም የመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ድርሻ ከ20 በመቶ እንደማያልፍ ተናግረዋል።

በመሆኑም መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋትና ለአምራቾች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ምጣኔውን ለማሳደግ በትኩረት እንሠራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን በማጠናከር የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ከማፋጠን ባለፈ ለዜጎች የሥራ ዕድል ስለሚፈጥር ተገቢ ትኩረት ይሰጠዋል ሲሉም ገልጸዋል።

በተለይ ክልሉ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብዓቶች በስፋት የሚመረትበት መሆኑን ጠቅሰው የግብርና ውጤቶች ዕሴት ተጨምሮባቸው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢኖቬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ጋግያብ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በክልሉ ከ340 በላይ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ6ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፣ በቀጣይ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አምራች ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት።

በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን ለሦስት ቀናት የሚቆይ አውደ ርዕይና ባዛርም ተከፍቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም