ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 30/2017(ኢዜአ)፦ ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የሰላም፣ የአብሮነትና የልማት ጉባኤ ግንቦት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስታወቀ።
የጉባኤው ጠቅላይ ጸሃፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ኩነቱን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ዓለም አቀፍ የሰላምና የአብሮነት ጉባኤው ከጂ 20 ኢንተር ፌዝ ፎረም፣ ከአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካ ህብረት ስር ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር የተዘጋጀ እንደሆነም ገልጸዋል።
የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዓለም አቀፍ የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራን፣ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መሪዎችና ሌሎችም ይሳተፋሉ።
በተጨማሪም ጉባዔው በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ግቦች፣ በአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እና በቀጣይ መስከረም በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የ2025 የቡድን 20 አባል አገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።
ጉባኤው ከቡድን 20 አባል አገራት የመሪዎች ጉባኤ አስቀድሞ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከጉባኤው የሚወጡ ምክረ ሃሳቦች ለአባል አገራት ስብሰባ እንደሚያቀርብ ተናግረዋል።
በሰላም ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ በትምህርትና ሌሎች የልማት አጀንዳዎች ዙሪያ በመምከር ለቡድን 20 አባል አገራት ምክረ ሃሳብ የሚያቀርብ ይሆናል።
በጉባኤው ከሰሜን አሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከእስያ፣ ከአፍሪካና ሌሎች የዓለም አገራት ከ80 በላይ የሚሆኑ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የባህል መሪዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ምሁራን ይሳተፋበታል ብለዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የሃይማኖት መከባበርና የአብሮነት ልምድ ይቀስማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቀሲሰ ታጋይ አንስተዋል።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችና ታሪካዊ ቦታዎችን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጨምረዋል።
የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገር ውስጥ በሰላምና መከባበር እሴት ግንባታ ላይ ከሚያከናውነው ተግባር በተጨማሪ ኢትዮጵያ የአፍሪካን አጀንዳ በማስተጋባት ያላትን ሚና እንድትቀጥል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል።